ኢዮብ 41:1-14 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. “ሌዋታንን በመንጠቆ ልታወጣው፣ወይም ምላሱን በገመድ ልታስረው ትችላለህን?

2. መሰነጊያ በአፍንጫው ልታስገባ፣ወይም ጒንጩን በሜንጦ ልትበሳ ትችላለህን?

3. እርሱ እንድትምረው ይለማመጥሃል?በለስላሳ ቃላትስ ይናገርሃል?

4. ለዘላለም ባሪያ ታደርገው ዘንድ፣ከአንተ ጋር ይዋዋላልን?

5. እንደ ወፍ አልምደኸው ከእርሱ ጋር ልትጫወት ትችላለህ?ወይስ ለሴት አገልጋዮችህ መጫወቻነት ታስረዋለህን?

6. ነጋዴዎችስ በእርሱ ላይ ይከራከራሉን?ለቸርቻሪዎችስ ያከፋፍሉታል?

7. ቈዳው ላይ አንካሴ ልትሰካ፣ጭንቅላቱንም በዓሣ መውጊያ ጦር ልትበሳ ትችላለህን?

8. እርሱን እስቲ ንካው፣ግብግቡን ታስታውሳለህ፤ ከቶም አያላምድህም።

9. እርሱን በቍጥጥር ሥር አውላለሁ ማለት ዘበት ነው፤በዐይን ማየት እንኳ ብርክ ያስይዛል።

10. ሊቀሰቅሰው የሚደፍር የለም፤ማን ፊቱ ሊቆም ይችላል?

11. ነክቶት በሰላም የሚሄድ ማን ነው?ከሰማይ በታች ማንም የለም።

12. “ስለ ብርታቱና ስለ አካላቱ ውበት፣ስለ እጅና እግሩ ከመናገር አልቈጠብም።

13. የደረበውን ልብስ ማን ሊያወልቅ ይችላል?ማንስ ሊለጒመው ወደ መንጋጋው ይቀርባል?

14. አስፈሪ ጥርሶቹ የተገጠገጡበትን፣የአፉን ደጅ ማን ደፍሮ ይከፍታል?

ኢዮብ 41