ኢዮብ 39:5-20 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

5. “ለሜዳ አህያ ነጻነት የሰጠው ማን ነው?እስራቱንስ ማን ፈታለት?

6. ምድረ በዳውን መኖሪያው፣የጨውንም ምድር ማደሪያው አድርጌ ሰጠሁት።

7. በከተማ ውካታ ይሥቃል፤የነጂውንም ጩኸት አይሰማም።

8. በየተራራው ይሰማራል፤ሐመልማሉንም ሁሉ ለማግኘት ይወጣል።

9. “ጐሽ ያገለግልህ ዘንድ ይታዘዛልን?በበረትህስ አጠገብ ያድራልን?

10. እንዲያርስልህ ልትጠምደው ትችላለህ?ወይስ እየተከተለህ ዕርሻህን ይጐለጒልልሃልን?

11. ጒልበቱ ብርቱ ስለ ሆነ ትተማመንበታለህ?ከባዱን ሥራህንስ ለእርሱ ትተዋለህ?

12. እህልህን እንዲሰበስብልህ፣በዐውድማህም ላይ እንዲያከማችልህ ታምነዋለህን?

13. “ሰጎን ክንፎቿን በደስታ ታራግባለች፤ነገር ግን እንደ ሽመላ ላባዎች ሊሆኑ አይችሉም።

14. ዕንቍላሏን መሬት ላይ ትጥላለች፤እንዲሞቅም በአሸዋ ውስጥ ትተወዋለች።

15. እግር እንደሚሰብረው፤የዱር አውሬም እንደሚረግጠው አታስብም።

16. የእርሷ እንዳልሆኑ ሁሉ በልጆቿ ትጨክናለች፤ድካሟም በከንቱ ቢቀር ደንታ የላትም፤

17. እግዚአብሔር ጥበብ ነሥቶአታልና፤ማስተዋልንም አልሰጣትም።

18. ለመሸምጠጥም ክንፎቿን ስትዘረጋ፣በፈረስና በጋላቢው ትሥቃለች።

19. “ለፈረስ ጒልበትን ትሰጠዋለህን?ዐንገቱንስ ጋማ ታለብሰዋለህን?

20. እንደ አንበጣ የምታስዘልለው አንተ ነህን?የማንኰራፋቱም ገናናነት አስፈሪ ነው።

ኢዮብ 39