ኢዮብ 39:17-30 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

17. እግዚአብሔር ጥበብ ነሥቶአታልና፤ማስተዋልንም አልሰጣትም።

18. ለመሸምጠጥም ክንፎቿን ስትዘረጋ፣በፈረስና በጋላቢው ትሥቃለች።

19. “ለፈረስ ጒልበትን ትሰጠዋለህን?ዐንገቱንስ ጋማ ታለብሰዋለህን?

20. እንደ አንበጣ የምታስዘልለው አንተ ነህን?የማንኰራፋቱም ገናናነት አስፈሪ ነው።

21. በጒልበቱ እየተመካ በብርቱ ይጐደፍራል፤ጦርነት ሊገጥም ይወጣል።

22. ያለ አንዳች ሥጋት፣ በፍርሀት ላይ ይሥቃል፤ሰይፍ ቢመዘዝበትም ወደ ኋላ አይልም።

23. ከሚብረቀረቀው ጦርና አንካሴ ጋር፣የፍላጻው ኮረጆ ጐኑ ላይ ይንኳኳል።

24. በወኔ መሬቱን እየጐደፈረ ወደ ፊት ይሸመጥጣል፤የመለከት ድምፅ ሲሰማ ያቅበጠብጠዋል።

25. መለከቱ ሲያንባርቅ፣ ‘እሰይ’ ይላል፤የአዛዦችን ጩኸትና የሰራዊቱን ውካታ፣ጦርነትንም ከሩቅ ያሸታል።

26. “ጭልፊት የሚበረው፣ክንፎቹንም ወደ ደቡብ የሚዘረጋው፣ በአንተ ጥበብ ነውን?

27. ንስር ወደ ላይ የሚመጥቀው፣ጎጆውንም በከፍታ ላይ የሚሠራው፣በአንተ ትእዛዝ ነውን?

28. በገደል ላይ ይኖራል፤ በዚያም ያድራል፤ምሽጉም የቋጥኝ ጫፍ ነው።

29. እዚያ ሆኖ የሚነጥቀውን ይቃኛል፤ዐይኑም ከሩቅ አጥርቶ ያያል።

30. ጫጩቶቹ ደም ይጠጣሉ፤እርሱም በድን ካለበት አይታጣም።”

ኢዮብ 39