6. ስለዚህ የቡዛዊው የባርክኤል ልጅ ኤሊሁ እንዲህ አለ፤“እኔ በዕድሜ ታናሽ ነኝ፤እናንተ ግን አዛውንቶች ናችሁ፤ከዚህም የተነሣ የማውቀውን ለመናገር አልደፈርሁም፤ፈርቼ ዝም አልሁ።
7. ‘ዕድሜ ይናገራል፤ረጅም ዘመን ጥበብን ያስተምራል’ ብዬ ነበር።
8. ነገር ግን በሰው ያለው መንፈስ፣ሁሉን የሚችል አምላክ እስትንፋስ፣ማስተዋልን ይሰጣል።
9. ጠቢባን የሚሆኑት በዕድሜ የገፉ ብቻ አይደሉም፤የሚያስተውሉም ሽማግሌዎች ብቻ አይደሉም።
10. “ስለዚህ፣ ‘ስሙኝ፣እኔም የማውቀውን ልንገራችሁ’ እላለሁ።
11. እናንተ በምትነጋገሩበት ጊዜ ታገሥሁ፤ቃላት እየመረጣችሁ ስትናገሩ፣በጥሞና ሰማኋችሁ፤
12. በሙሉ ልብ አዳመጥኋችሁ፤ነገር ግን ከእናንተ የኢዮብን ቃል ያስተባበለ ማንም የለም፤ለንግግሩም አጸፋ የመለሰ አልተገኘም።