ኢዮብ 28:6-17 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

6. ሰንፔር ከዐለቷ ይወጣል፤ከዐፈሯም የወርቅ አንኳር ይገኛል።

7. ያን መንገድ ጭልፊት አያውቀውም፤የአሞራም ዐይን አላየውም፣

8. ኵሩ አራዊት አልረገጡትም፤አንበሳም በዚያ አላለፈም።

9. ሰው እጁን በቡላድ ድንጋይ ላይ ያነሣል፤ተራሮችንም ከሥር ይገለብጣል።

10. በድንጋይ ውስጥ መተላለፊያ ያበጃል፤ዐይኖቹም የከበሩ ነገሮችን ሁሉ ያያሉ።

11. የወንዞችን ምንጭ ይበረብራል፤የተሰወረውንም ነገር ወደ ብርሃን ያወጣል።

12. “ነገር ግን ጥበብ ከወዴት ትገኛለች?ማስተዋልስ መኖሪያዋ የት ነው?

13. ሰው ዋጋዋን አያውቅም፤በሕያዋንም ምድር አትገኝም።

14. ውቅያኖስ፣ ‘በእኔ ውስጥ የለችም’ ይላል፤ባሕርም፣ ‘በእኔ ዘንድ አይደለችም’ ይላል።

15. ንጹሕ ወርቅ ሊገዛት አይችልም፤ዋጋዋም በብር አይመዘንም።

16. በኦፊር ወርቅ፣በከበረም መረግድና በሰንፔር አትገመትም።

17. ወርቅም ብርሌም አይወዳደሯትም፤በወርቅ ጌጥም አትለወጥም።

ኢዮብ 28