ኢዮብ 15:4-16 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

4. አንተ ግን እግዚአብሔርን መፍራት ታጣጥላለህ፤አምልኮተ እግዚአብሔርን ትከለክላለህ።

5. ኀጢአትህ አፍህን ታስተምረዋለች፤የተንኰለኞችንም አነጋገር መርጠህ ትይዛለህ።

6. የሚፈርድብህ አንደበትህ እንጂ እኔ አይደለሁም፣የሚመሰክርብህም እኔ ሳልሆን የገዛ ከንፈርህ ነው።

7. “ለመሆኑ ከሰው ሁሉ ቀድመህ የተወለድህ አንተ ነህን?ወይስ ከኰረብቶች በፊት ተገኝተሃል?

8. በእግዚአብሔር የመማክርት ጉባኤ ላይ ነበርህን?ጥበብስ የተሰጠው ለአንተ ብቻ ነው?

9. እኛ የማናውቀው አንተ ግን የምታውቀው ምን ነገር አለ?እኛስ የሌለን አንተ ያለህ ማስተዋል የቱ ነው?

10. በዕድሜ ከአባትህ የሚበልጡ፣የሸበቱ ሽማግሌዎች ከእኛ ጋር አሉ።

11. የእግዚአብሔር ማጽናናት፣በርጋታ የተነገረህ ቃል አነሰህን?

12. ልብህ ለምን ይሸፍታል?ዐይንህንስ ምን ያጒረጠርጠዋል?

13. በእግዚአብሔር ላይ እንድትቈጣ፣እንደዚህ ያለ ቃል ከአፍህ እንዲወጣ ያደረገህ ምንድን ነው?

14. “ንጹሕ ይሆን ዘንድ ሰው ምንድን ነው?ጻድቅስ ይሆን ዘንድ፣ ከሴት የተወለደ ምንድን ነው?

15. እነሆ፤ እግዚአብሔር በቅዱሳኑ እንኳ አይታመንም፤ሰማያትም በእርሱ ፊት ንጹሓን አይደሉም።

16. ታዲያ፣ ክፋትን እንደ ውሃ የሚጠጣ!አስጸያፊና ርኩስ ሰውማ እንዴት ይታመን!

ኢዮብ 15