ኢዮብ 14:3-12 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

3. እንደዚህ ባለ ሰው ላይ ዐይንህን ታሳርፋለህን?ለፍርድስ በፊትህ ታቀርበዋለህን?

4. ከርኩስ ነገር ውስጥ ንጹሕን ማን ሊያወጣ ይችላል?አንድ እንኳ የሚችል የለም!

5. የሰው ዕድሜ አስቀድሞ የተወሰነ ነው፣የወራቱንም ብዛት ወስነህ አስቀምጠሃል፤ሊያልፈው የማይችለውንም ገደብ አኖርህለት።

6. እንግዲህ ዘመኑን እንደ ምንደኛ እስኪፈጽም ድረስ፣ፊትህን ከእርሱ መልስ፤ ተወው።

7. “ዛፍ እንኳ ቢቈረጥ፣እንደ ገና ሊያቈጠቍጥ፣አዳዲስ ቅርንጫፍም ሊያበቅል ተስፋ አለው።

8. ሥሩ በምድር ውስጥ ቢያረጅጒቶው በመሬት ውስጥ ቢበሰብስም፣

9. የውሃ ሽታ ባገኘ ጊዜ ያቈጠቍጣል፤እንደ ተተከለም ችግኝ ቅርንጫፍ ያወጣል።

10. ሰው ግን ይሞታል፤ ክንዱንም ይንተራሳል፤ነፍሱም ትወጣለች፤ ከእንግዲህስ የት ይገኛል?

11. ውሃ ከባሕር ውስጥ እንደሚያልቅ፣የወንዝ ውሃም ጠፍቶ እንደሚደርቅ፣

12. እንደዚሁም ሰው ይተኛል ቀናም አይልም፤ሰማይ እስከሚያልፍ ድረስ አይነቃም፤ከእንቅልፉም አይነሣም።

ኢዮብ 14