ኢዮብ 13:11-25 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

11. ግርማው አያስደነግጣችሁምን?ክብሩስ አያስፈራችሁምን?

12. ምሳሌዎቻችሁ የዐመድ ምሳሌዎች ናቸው፣መከላከያችሁም የጭቃ ምሽግ ነው።

13. “ዝም በሉ፤ እኔ ልናገር፤የመጣው ይምጣብኝ።

14. ሥጋዬን በጥርሴ፣ሕይወቴንም በእጄ ለምን እይዛለሁ?

15. ቢገድለኝም እንኳ በእርሱ ተስፋ አደርጋለሁ፤ስለ መንገዴም ፊት ለፊት እከራከረዋለሁ።

16. ኀጢአተኛ በእርሱ ፊት መቅረብ ስለማይችል፤ይህ ድፍረቴ ለመዳኔ ይሆናል።

17. ቃሌን በጥንቃቄ አድምጡ፤እኔ የምለውንም ጆሮአችሁ በሚገባ ይስማ፤

18. እንግዲህ ጒዳዬን ይዤ ቀርቤአለሁ፤እንደሚፈርድልኝም ዐውቃለሁ።

19. ሊከሰኝ የሚችል አለ?ካለም፣ ዝም ብዬ ሞቴን እጠብቃለሁ።

20. “አምላክ ሆይ እነዚህን ሁለት ነገሮች ብቻ ስጠኝ፣ያን ጊዜ ከፊትህ አልሰወርም፤

21. እጅህን ከእኔ ላይ አንሣ፤በግርማህም አታስፈራራኝ፤

22. ከዚያ በኋላ ጥራኝ፤ እኔም እመልስልሃለሁ፤ወይም እኔ ልናገር፤ አንተ መልስልኝ።

23. በደሌና ኀጢአቴ ምን ያህል ነው?መተላለፌንና ኀጢአቴን አስታውቀኝ።

24. ፊትህን ለምን ትሰውራለህ?እንደ ጠላትህስ ለምን ትቈጥረኛለህ?

25. ነፋስ ያረገፈውን ቅጠል ታስጨንቃለህን?የደረቀውንስ እብቅ ታሳድዳለህን?

ኢዮብ 13