ኢያሱ 23:4-9 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

4. ከዮርዳኖስ አንሥቶ በስተ ምዕራብ እስካለው እስከ ታላቁ ባሕር ድረስ በሙሉ ካሸነፍኋቸው ሕዝቦች ያልወረሳችሁትን ቀሪ ምድር ርስት እንዲሆን ለየነገዶቻችሁ እንዴት አድርጌ በዕጣ እንዳከፋፈልኋችሁ አስታውሱ።

5. ራሱ አምላካችሁ እግዚአብሔር ከፊታችሁ ያስወግዳቸዋል፤ ከፊታችሁም ያሉበትን ስፍራ ያስለቅቃቸዋል፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር በሰጣችሁም ተስፋ መሠረት ምድራቸውን ትወርሳላችሁ።

6. “በርቱ፤ ወደ ግራም ወደ ቀኝም ሳትሉ በሙሴ የሕግ መጽሐፍ የተጻፈውን ሁሉ ለመጠበቅና ለማድረግ እጅግ በርቱ።

7. በመካከላችሁ ከቀሩት ከእነዚህ ሕዝቦች ጋር አትተባበሩ፤ የአማልክቶቻቸውን ስም አትጥሩ፤ አትማሉባቸው፤ አታገልግሏቸው፤ አትስገዱላቸውም፤

8. ነገር ግን እስካሁን እንዳደረጋችሁት ሁሉ አምላካችሁን እግዚአብሔርን አጥብቃችሁ ያዙ።

9. “እግዚአብሔር ታላላቅና ኀያላን ሕዝቦችን ከፊታችሁ አሳድዶ አስወጥቶአቸዋል፤ እስከ ዛሬም ድረስ ማንም ሊቋቋማችሁ አልቻለም።

ኢያሱ 23