ኢያሱ 22:1-21 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. በዚህ ጊዜ ኢያሱ የሮቤልንና የጋድን ነገዶች፣ እንዲሁም የምናሴን ነገድ እኩሌታ ጠርቶ፣

2. እንዲህ አላቸው፤ “የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ ያዘዘውን ሁሉ ጠብቃችኋል፤ እኔም ያዘዝኋችሁን በሙሉ ፈጽማችኋል፤

3. ከረጅም ጊዜ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ወንድሞቻችሁን አልተዋችሁም፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር የሰጣችሁን ተልእኮ በሚገባ ተወጥታችኋል።

4. አሁንም አምላካችሁ እግዚአብሔር በሰጣችሁ ተስፋ መሠረት ወንድሞቻችሁን አሳርፎአቸዋል፤ ስለዚህ የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ ከዮርዳኖስ ማዶ ርስት አድርጎ በሰጣችሁ ምድር ወዳለው ቤታችሁ ተመለሱ።

5. የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ፣ አምላካችሁን እግዚአብሔርን እንድትወዱ፣ በመንገዱ ሁሉ እንድትሄዱ፣ ትእዛዙን እንድትፈጽሙ፣ እርሱንም አጥብቃችሁ እንድትይዙት እንዲሁም በፍጹም ልባችሁ፣ በፍጹም ነፍሳችሁ እንድታገለግሉት የሰጣችሁን ትእዛዙንና ሕጉን ነቅታችሁ ጠብቁ።”

6. ከዚያም ኢያሱ መርቆ አሰናበታቸው፤ እነርሱም ወደ ቤታቸው ተመለሱ።

7. ሙሴ ለምናሴ ነገድ እኩሌታ በባሳን ምድር ርስት ሰጥቶአቸው ነበር፤ ለቀረው እኩሌታ ደግሞ ኢያሱ ከዮርዳኖስ በስተ ምዕራብ ከወንድሞቻቸው ጋር ርስት ሰጣቸው። ኢያሱ ወደ ቤታቸው እንዲገቡ ባሰናበታቸው ጊዜ መረቃቸው፤

8. እንዲህም አላቸው፤ “ብዙ ሀብት ይዛችሁ ማለትም አያሌ የከብት መንጋ፣ ብርና ወርቅ፣ ናስና ብረት እንዲሁም ቊጥሩ እጅግ የበዛ ልብስ ይዛችሁ ወደ ቤታችሁ ተመለሱ፤ ከጠላት የተገኘውንም ይህን ምርኮ ከወንድሞቻችሁ ጋር ተካፈሉት” አላቸው።

9. ስለዚህ የሮቤልና የጋድ ነገዶች እንዲሁም የምናሴ ነገድ እኩሌታ እስራኤላውያንን ከነዓን ውስጥ ባለችው በሴሎ ትተው፣ በእግዚአብሔር ትእዛዝ በሙሴ አማካይነት ወደ ተቀበሏት ርስታቸው፣ ወደ ገለዓድ ምድር ተመለሱ።

10. የሮቤልና የጋድ እንዲሁም የምናሴ ነገድ እኩሌታ በከነዓን ምድር ወዳለችው፣ ዮርዳኖስ አጠገብ ወደምትገኘው ገሊሎት ወደተባለች ስፍራ ሲደርሱ በወንዙ አጠገብ ግዙፍ መሠዊያ ሠሩ።

11. የእስራኤላውያን ይዞታ በሆነችው በከነዓናውያን ምድር ወሰን በገሊሎት ላይ መሠዊያ መሥራታቸውን፣ ሌሎቹ እስራኤላውያን በሰሙ ጊዜ፣

12. በእነርሱ ላይ ለመዝመት፣ የእስራኤል ማኅበር ሁሉ በሴሎ ተሰበሰቡ።

13. ስለዚህም እስራኤላውያን የካህኑ የአልዓዛርን ልጅ ፊንሐስን በገለዓድ ምድር ወደሚኖሩት ወደ ሮቤልና ወደ ጋድ እንዲሁም ወደ ምናሴ ነገድ እኩሌታ ላኩ፤

14. ከእርሱም ጋር እያንዳንዱን የእስራኤልን ነገድ የሚወክሉ ዐሥር አለቆች አብረው ላኩ፤ እነዚህም እያንዳንዳቸው ከእስራኤላውያን ጐሣዎች የተውጣጡ የየቤተ ሰቡ አለቆች ነበሩ።

15. እነርሱም በገለዓድ ምድር ወዳሉት ወደ ሮቤላውያን፣ ወደ ጋዳውያንና ወደ ምናሴ ነገድ እኩሌታ ሄደው እንዲህ አሏቸው፤

16. “መላው የእግዚአብሔር ጉባኤ እንዲህ ይላል፤ ‘በእስራኤል አምላክ ላይ እንዲህ ያለ ክህደት የፈጸማችሁት ለምንድን ነው? እግዚአብሔርን ከመከተልስ እንዴት ወደ ኋላ ትላላችሁ? እንዴትስ ዛሬ በእግዚአብሔር ላይ ዐምፃችሁ ለራሳችሁ መሠዊያ ትሠራላችሁ?

17. በፌጎር የተሠራው ኀጢአት አይበቃንምን? ምንም እንኳ በእግዚአብሔር ጉባኤ ላይ መቅሠፍት ቢወርድም፣ እስከ ዛሬዪቱ ዕለት ድረስ ራሳችንን ከዚያች ኀጢአት አላነጻንም።

18. እናንተ፣ አሁንም እግዚአብሔርን ከመከተል ወደ ኋላ ትላላችሁን?“ ‘ዛሬ እናንተ በእግዚአብሔር ላይ ብታምፁ፣ እርሱ ደግሞ ነገ በመላው እስራኤል ጉባኤ ላይ ይቈጣል።

19. የወረሳችኋት ምድር ረክሳ እንደሆነ፣ የእግዚአብሔር ማደሪያ ወደ ተተከለበት ወደ እግዚአብሔር ምድር መጥታችሁ ከእኛ ጋር ርስት ተካፈሉ፤ ነገር ግን ከአምላካችን ከእግዚአብሔር መሠዊያ በስተቀር ሌላ መሠዊያ ሠርታችሁ በእግዚአብሔርም ሆነ በእኛ ላይ አታምፁ።

20. የዛራ ልጅ አካን፣ እርም የሆነውን ነገር በመውሰድ ኀጢአት ስለ ሠራ፣ በመላው የእስራኤል ጉባኤ ላይ ቍጣ አልመጣምን? በሠራው ኀጢአት የሞተውም እርሱ ብቻ አልነበረም።”

21. ከዚያም የሮቤልና የጋድ ነገዶች እንዲሁም የምናሴ ነገድ እኩሌታ ለእስራኤል ጐሣ መሪዎች እንዲህ ሲሉ መለሱላቸው፤

ኢያሱ 22