ኢያሱ 13:6-20 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

6. “ከሊባኖስ እስከ ማሴሮን ባለው ተራራማ ምድር ላይ የሚኖሩትን ሁሉ፣ ሲዶናውያንንም ጭምር እኔው ራሴ ከእስራኤላውያን ፊት አሳድጄ አስወጣቸዋለሁ። ብቻ አንተ ባዘዝሁህ መሠረት ምድሪቱን ርስት አድርገህ ለእስራኤላውያን አካፍል።

7. ይህንንም ለዘጠኙ ነገድና ለምናሴ ነገድ እኩሌታ ርስት አድርገህ አካፍል።”

8. ሌላው የምናሴ ነገድ እኩሌታ፣ የሮቤል ነገድና የጋድ ነገድ የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ እንደየ ድርሻቸው ከፋፍሎ በመደበላቸው መሠረት፣ ራሱ ሙሴ የሰጣቸውን ርስት ተቀበሉ።

9. ይህም ከአርኖን ሸለቆ ዳርቻ ካለው ከአሮዔርና በሸለቆው መካከል ካለችው ከተማ አንሥቶ እስከ ዲቦን የሚደርሰውን የሜድባን ደጋማ ምድር በሙሉ ይይዛል፤

10. እንዲሁም በሐሴቦን ተቀምጦ እስከ አሞናውያን ዳርቻ የገዛውን የአሞራውያንን ንጉሥ የሴዎንን ከተሞች ሁሉ ያጠቃልላል፤

11. በተጨማሪም ገለዓድን፣ የጌሹራውያንንና የማዕካታውያንን ግዛት ሁሉ፣ የአርሞንዔምን ተራራ በሙሉ፣ ባሳንንም ሁሉ እስከ ሰልካ ድረስ ይይዛል፤

12. ይህም በአስታሮትና በኤድራይ ሆኖ የገዛውን በባሳን ያለውን የዐግን መንግሥት በሙሉ ያጠቃልላል፤ ዐግም በሕይወት ከቀሩት ከመጨረሻዎቹ ከራፋይም ዘሮች አንዱ ነበር፤ እነዚህንም ሙሴ ድል አደረጋቸው፤ ምድራቸውንም ያዘ፤

13. ነገር ግን እስራኤላውያን የጌሹርንና የማዕካትን ሕዝብ ስላላስወጡ፣ እስከ ዛሬ ድረስ በመካከላቸው ይኖራሉ።

14. ለሌዊ ነገድ ግን ርስት አልሰጠም፤ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር በእሳት የሚቀርበው ቊርባን፣ በተሰጣቸው ተስፋ መሠረት ርስታቸው ነውና።

15. ሙሴ በየጐሣቸው መድቦ ለሮቤል ነገድ የሰጠው ርስት ይህ ነው፤

16. ድንበራቸው ከአርኖን ሸለቆ ዳርቻ ካለው ከአሮዔርና ከሸለቆው መካከል ካለችው ከተማ አንሥቶ ያለው ግዛት ሲሆን፣ ሜድባ አጠገብ ያለውን ደጋውን አገር በሙሉ፣

17. ሐሴቦንና በደጋው ላይ ያሉትን ከተሞችዋን በሙሉ፣ እንዲሁም ዲቦንን፣ ባሞትባኣልን፣ ቤትበኣልምዖን፣

18. ያሀጽን፣ ቅዴሞትን፣ ሜፍዓትን፣

19. ቂርያታያምን፣ ሴባማን፣ በሸለቆው ኰረብታ ላይ ያለችውን ጼሬትሻሐርን፣

20. ቤተፌጎርን፣ የፈስጋን ሸንተረሮችና ቤትየሺሞትን፣

ኢያሱ 13