14. ለሌዊ ነገድ ግን ርስት አልሰጠም፤ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር በእሳት የሚቀርበው ቊርባን፣ በተሰጣቸው ተስፋ መሠረት ርስታቸው ነውና።
15. ሙሴ በየጐሣቸው መድቦ ለሮቤል ነገድ የሰጠው ርስት ይህ ነው፤
16. ድንበራቸው ከአርኖን ሸለቆ ዳርቻ ካለው ከአሮዔርና ከሸለቆው መካከል ካለችው ከተማ አንሥቶ ያለው ግዛት ሲሆን፣ ሜድባ አጠገብ ያለውን ደጋውን አገር በሙሉ፣
17. ሐሴቦንና በደጋው ላይ ያሉትን ከተሞችዋን በሙሉ፣ እንዲሁም ዲቦንን፣ ባሞትባኣልን፣ ቤትበኣልምዖን፣
18. ያሀጽን፣ ቅዴሞትን፣ ሜፍዓትን፣
19. ቂርያታያምን፣ ሴባማን፣ በሸለቆው ኰረብታ ላይ ያለችውን ጼሬትሻሐርን፣
20. ቤተፌጎርን፣ የፈስጋን ሸንተረሮችና ቤትየሺሞትን፣
21. ማለት በደጋው አገር የሚገኙት ከተሞች ሁሉና መቀመጫውን በሐሴቦን አድርጎ የገዛውን የአሞራውያንን ንጉሥ የሴዎንን ግዛት በሙሉ ያካትታል። ሙሴ ሴዎንንና በዚያው ምድር ተቀማጭ የነበሩትን መሳፍንት፤ አዊ፣ ሮቆም፣ ሱር፣ ሑርና ሪባ የተባሉትን የምድያም አለቆች ድል አደረጋቸው።
22. በጦር ሜዳ ከሞቱት ሌላ እስራኤላውያን የቢዖርን ልጅ ምዋርተኛውን በለዓምን በሰይፍ መትተው ገደሉት።
23. የሮቤል ነገድ ወሰን የዮርዳኖስ ወንዝ ነው፤ የሮቤል ነገድ በየጐሣቸው የወረሷቸው ከተሞችና መንደሮቻቸው እነዚህ ነበሩ፤
24. ሙሴ በየጐሣቸው መድቦ ለጋድ ነገድ የሰጠው ርስት ይህ ነው፤
25. ድንበራቸው ኢያዜር፣ የገለዓድን ከተሞች በሙሉ በረባት አጠገብ እስካለው እስከ አሮዔር የሚደርሰውን የአሞናውያን አገር እኩሌታ፣
26. ከሐሴቦን እስከ ራማት ምጽጴና ከዚያም እስከ ብጦኒም፣ ከመሃናይም እስከ ደቤር ግዛት ያለውን፣
27. በሸለቆው ውስጥ ደግሞ ቤትሀራምን፣ ቤትኒምራን፣ ሱኮትን፣ ዳፎንንና እስከ ኪኔሬት ባሕር ጫፍ የሚደርሰውን ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ ያለውን ቀሪውን የሐሴቦን ንጉሥ የሴዎንን ግዛት ያካትታል፤
28. የጋድ ነገድ በየጐሣቸው የወረሷቸው ከተሞችና መንደሮቻቸው እነዚህ ነበሩ።