ኢያሱ 10:21-31 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

21. ከዚያም ሰራዊቱ ሁሉ በደኅና ተመልሶ፣ ኢያሱ ወደ ሰፈረበት ወደ መቄዳ መጣ፤ በእስራኤላውያንም ላይ አንዲት ቃል የተናገረ ሰው አልነበረም።

22. ኢያሱም፤ “ዋሻውን ከፍታችሁ እነዚያን አምስቱን ነገሥታት አውጥታችሁ አምጡልኝ” አላቸው።

23. እነርሱም አምስቱን ነገሥታት ማለትም የኢየሩሳሌምን ንጉሥ፣ የኬብሮንን ንጉሥ፣ የያርሙትን ንጉሥ፣ የለኪሶን ንጉሥ የዔግሎንን ንጉሥ አውጥተው አመጡለት።

24. እነዚህን ነገሥታት ባመጡለትም ጊዜ፣ ኢያሱ መላውን የእስራኤልን ወንዶች ከጠራ በኋላ አብረውት የመጡትን የጦር አዛዦች፣ “ወደዚህ ቅረቡና እግሮቻችሁን በእነዚህ ነገሥታት አንገት ላይ አድርጉ” አላቸው፤ እነርሱም ወደ ፊት ቀርበው እግራቸውን በነገሥታቱ አንገት ላይ አሳረፉ።

25. ኢያሱም፣ “አትፍሩ፤ አትደንግጡ፤ በርቱ፤ ጽኑ፤ እንግዲህ በምትወጓቸው ጠላቶች ሁሉ ላይ እግዚአብሔር እንደዚሁ ያደርጋልና” አላቸው።

26. ከዚያም ኢያሱ ነገሥታቱን መትቶ ገደላቸው፤ በአምስትም ዛፎች ላይ ሰቀላቸው፤ ሬሳቸውም እስኪመሽ ድረስ አልወረደም ነበር።

27. ፀሓይ ለመጥለቅ በማዘቅዘቅ ላይ ሳለች ኢያሱ ትእዛዝ ሰጠ፤ ከዚያም የነገሥታቱን ሬሳ ከዛፎቹ ላይ አውርደው ቀድሞ ተደብቀው ወደነበሩበት ዋሻ ውስጥ ጣሏቸው። በዋሻውም አፍ ትልልቅ ድንጋዮች አኖሩ፤ ድንጋዮቹም እስከ ዛሬ ድረስ በዚያ ይገኛሉ።

28. በዚያች ዕለት ኢያሱ መቄዳን ያዘ፤ ከተማዪቱንና ንጉሥዋንም በሰይፍ ስለት መታ፤ አንድም ሰው ሳያስቀር በውስጧ ያለውን ሁሉ ፈጽሞ ደመሰሰ፤ በኢያሪኮ ንጉሥ ላይ ያደረገውንም ሁሉ፣ በመቄዳ ንጉሥ ላይ አደረገ።

29. ከዚያም ኢያሱና ከእርሱ ጋር የነበሩት እስራኤላውያን በሙሉ ከመቄዳ ወደ ልብና አለፉ፤ ወጓትም።

30. እንዲሁም እግዚአብሔር ከተማዪቱንና ንጉሥዋን በእስራኤል እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፤ ኢያሱ ከተማዪቱንና በውስጧ ያለውን ሁሉ በሰይፍ ስለት አጠፋ፤ አንድም ሰው አላስተረፈም፤ በኢያሪኮ ንጉሥ ላይ ያደረገውንም በልብና ንጉሥ ላይ ደገመው።

31. ከዚያም ኢያሱና ከእርሱ ጋር የነበሩት እስራኤላውያን በሙሉ ከልብና ወደ ለኪሶ አለፉ፤ ወጓትም።

ኢያሱ 10