ኢያሱ 10:15-25 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

15. ከዚያም ኢያሱ ከመላው እስራኤል ጋር ጌልገላ ወዳለው ሰፈር ተመለሰ።

16. በዚህ ጊዜ አምስቱ የአሞራውያን ነገሥታት ሸሽተው በመቄዳ ዋሻ ተደብቀው ነበር።

17. ኢያሱም አምስቱ ነገሥታት በመቄዳ ዋሻ ውስጥ ተደብቀው መገኘታቸውን ሰማ፣

18. እንዲህም አለ፤ “ትልልቅ ድንጋዮች ወደ ዋሻው አፍ አንከባሉ፤ ጠባቂ ሰዎችንም በዚያ አቁሙ፤

19. ጠላቶቻችሁን አሳዱአቸው እንጂ ችላ አትበሉ፤ ከበስተ ኋላ ሆናችሁም አደጋ ጣሉባቸው፤ ወደ ከተሞቻቸው እንዳይገቡ ከልክሏቸው፤ እነሆ፤ እግዚአብሔር አምላካችሁ በእጃችሁ አሳልፎ ሰጥቶአቸዋልና።”

20. ስለዚህ ኢያሱና እስራኤላውያን እስከ መጨረሻው ደመሰሷቸው፤ የተረፉት ጥቂቶቹ ግን ወደ ተመሸጉት ከተሞቻቸው ለመድረስ ቻሉ።

21. ከዚያም ሰራዊቱ ሁሉ በደኅና ተመልሶ፣ ኢያሱ ወደ ሰፈረበት ወደ መቄዳ መጣ፤ በእስራኤላውያንም ላይ አንዲት ቃል የተናገረ ሰው አልነበረም።

22. ኢያሱም፤ “ዋሻውን ከፍታችሁ እነዚያን አምስቱን ነገሥታት አውጥታችሁ አምጡልኝ” አላቸው።

23. እነርሱም አምስቱን ነገሥታት ማለትም የኢየሩሳሌምን ንጉሥ፣ የኬብሮንን ንጉሥ፣ የያርሙትን ንጉሥ፣ የለኪሶን ንጉሥ የዔግሎንን ንጉሥ አውጥተው አመጡለት።

24. እነዚህን ነገሥታት ባመጡለትም ጊዜ፣ ኢያሱ መላውን የእስራኤልን ወንዶች ከጠራ በኋላ አብረውት የመጡትን የጦር አዛዦች፣ “ወደዚህ ቅረቡና እግሮቻችሁን በእነዚህ ነገሥታት አንገት ላይ አድርጉ” አላቸው፤ እነርሱም ወደ ፊት ቀርበው እግራቸውን በነገሥታቱ አንገት ላይ አሳረፉ።

25. ኢያሱም፣ “አትፍሩ፤ አትደንግጡ፤ በርቱ፤ ጽኑ፤ እንግዲህ በምትወጓቸው ጠላቶች ሁሉ ላይ እግዚአብሔር እንደዚሁ ያደርጋልና” አላቸው።

ኢያሱ 10