ኢያሱ 10:1-9 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. የኢየሩሳሌም ንጉሥ አዶኒጼዴቅ፣ ኢያሱ ጋይን ይዞ እንደ ደመሰሳት፣ እንደዚሁም በኢያሪኮና በንጉሥዋ ላይ ያደረገውን ሁሉ፣ በጋይና በንጉሥዋ ላይ ማድረጉን፣ የገባዖን ሰዎችም ከእስራኤል ጋር የሰላም ውል አድርገው በአጠገባቸው መኖራቸውን ሰማ፤

2. በዚህም እርሱና ሕዝቡ ደነገጡ፤ ምክንያቱም ገባዖን እንደ ነገሥታቱ ከተማ ሁሉ ታላቅ ከተማ፣ በስፋቷም ከጋይ የምትበልጥ፣ ሰዎቿም ብርቱ ተዋጊዎች ነበሩ።

3. ስለዚህ የኢየሩሳሌም ንጉሥ አዶኒጼዴቅ፣ ሆሃም ወደተባለው የኬብሮን ንጉሥ ጲርአም ወደተባለው የየርሙት ንጉሥ፣ ያፊዓ ወደተባለው የለኪሶ ንጉሥና ዳቤር ወደተባለው የዔግሎን ንጉሥ በመላክ፣

4. “ወደዚህ ወጥታችሁ አግዙኝ፤ ከኢያሱና ከእስራኤላውያን ጋር ሰላምን መሥርታለችና ገባዖንን እንምታ” አላቸው።

5. ከዚያም አምስቱ የአሞራውያን ነገሥታት ማለት የኢየሩሳሌም ንጉሥ፣ የኬብሮን ንጉሥ፣ የያርሙት ንጉሥ፣ የለኪሶ ንጉሥና የዔግሎን ንጉሥ ያላቸውን አስተባብረው፣ ሰራዊታቸውንም ሁሉ ይዘው በመውጣት ገባዖንን ወጓት።

6. የገባዖንም ሰዎች በጌልገላ ወደ ሰፈረው ወደ ኢያሱ፣ “በተራራማው አገር የሚኖሩ የአሞራውያን ነገሥታት ኀይላቸውን አስተባብረው ተሰልፈውብናል፤ እኛን ባሮችህን አትተወን፤ ርዳን፤ ፈጥነህ በመድረስም አድነን” ሲሉ ላኩበት።

7. ስለዚህ ኢያሱ ምርጥ የሆኑትን ተዋጊዎች ሁሉ ጨምሮ ሰራዊቱን በሙሉ ይዞ ከጌልገላ ወጣ።

8. እግዚአብሔርም ኢያሱን፣ “አትፍራቸው፤ ሁሉንም አሳልፌ በእጅህ ሰጥቻቸዋለሁ፤ አንዳቸውም እንኳ ሊቋቋሙህ አይችሉም” አለው።

9. ኢያሱ ከጌልገላ ሌሊቱን ሁሉ ሲገሠግሥ አድሮ ድንገት ወረራቸው።

ኢያሱ 10