ኢሳይያስ 43:1-14 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. አሁን ግን፣ ያዕቆብ ሆይ! የፈጠረህ፤እስራኤል ሆይ! የሠራህ፣ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“ተቤዥቼሃለሁና አትፍራ፤በስምህ ጠርቼሃለሁ፤ አንተ የእኔ ነህ፤

2. በውሃ ውስጥ በምታልፍበት ጊዜ፣ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤ወንዙን ስትሻገረው፣አያሰጥምህም፤በእሳት ውስጥ ስትሄድ፣አያቃጥልህም፤ነበልባሉም አይፈጅህም።

3. እኔ እግዚአብሔር አምላክህ፣የእስራኤልም ቅዱስ መድኀኒትህ ነኝና፤ግብፅን ለአንተ ቤዛ እንድትሆን፣ኢትዮጵያንና ሳባን በአንተ ፈንታ እሰጣለሁ።

4. ለዐይኔ ብርቅና ክቡርም ስለ ሆንህ፣እኔም ስለምወድህ፣ሰዎችን በአንተ ምትክ፣ሕዝቦችንም በሕይወትህ ፈንታ እሰጣለሁ።

5. ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ፤ልጆችህን ከምሥራቅ አመጣለሁ፤ከምዕራብም እሰበስብሃለሁ።

6. ሰሜንን፣ ‘አምጣ’፣ደቡብንም፣ ‘ልቀቅ’ እላለሁ፤ወንዶች ልጆቼን ከሩቅ፣ሴቶች ልጆቼንም ከምድር ዳርቻ፣

7. በስሜ የተጠራውን ሁሉ፣ለክብሬ የፈጠርሁትን፣ያበጀሁትንና የሠራሁትን አምጡ።”

8. ዐይን እያላቸው የታወሩትን፣ጆሮ እያላቸው የደነቈሩትን አውጣ።

9. ሕዝብ ሁሉ በአንድነት ይሰብሰብ፤ሰውም ይከማች፤ከእነርሱ አስቀድሞ ይህን የነገረን፣የቀድሞውን ነገር ያወጀልን ማን ነው?ሌሎችን ሰምተው፣ “እውነት ነው” እንዲሉ፣ትክክለኝነታቸውም እንዲረጋገጥ ምስክሮቻቸውን ያቅርቡ።

10. “ታውቁና ታምኑብኝ ዘንድ፣እርሱ እኔ እንደሆንሁ ትረዱ ዘንድ፣እናንተ ምስክሮቼ፣የመረጥሁትም ባሪያዬ ናችሁ” ይላል እግዚአብሔር።“ከእኔ በፊት አምላክ አልተሠራም፤ከእኔም በኋላ አይኖርም።

11. እኔ፣ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ከእኔም ሌላ የሚያድን የለም።

12. ገልጫለሁ፤ አድኛለሁ፤ ተናግሬአለሁ፤በመካከላችሁ እኔ እንጂ ባዕድ አምላክ አልነበረም።እኔ አምላክ እንደሆንሁ፣ እናንተ ምስክሮቼ ናችሁ” ይላል እግዚአብሔር፤

13. “ከጥንት ጀምሮ እኔው ነኝ፤ከእጄም ማውጣት የሚችል የለም፤እኔ የምሠራውን ማን ማገድ ይችላል?”

14. የእስራኤል ቅዱስ፣የሚቤዣችሁ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“ስለ እናንተ በባቢሎን ላይ ሰራዊት እሰዳለሁ፤በሚመኩባቸውም መርከቦች፣ባቢሎናውያንን ሁሉ እንደ ኰብላይ አመጣለሁ።

ኢሳይያስ 43