15. እነሆ፤ አሕዛብ በገንቦ ውስጥ እንዳለች ጠብታ ናቸው፤በሚዛን ላይ እንዳለ ትቢያ ይቈጠራሉ፤ደሴቶችንም እንደ ደቃቅ ዐፈር ይመዝናቸዋል።
16. ሊባኖስ ለመሠዊያ እሳት አትበቃም፤የእንስሶቿም ቍጥር ለሚቃጠል መሥዋዕት ያንሳል።
17. አሕዛብ ሁሉ በፊቱ እንደ ኢምንት ናቸው፤ከምንም የማይቈጠሩ መና ናቸው።
18. እንግዲህ፣ እግዚአብሔርን ከማን ጋር ታወዳድሩታላችሁ?ከየትኛውስ ምስል ጋር ታነጻጽሩታላችሁ?
19. የተቀረጸውንማ ምስል ባለጅ ይቀርጸዋል፤ወርቅ አንጥረኛም በወርቅ ይለብጠዋል፤የብር ሰንሰለትም ያበጅለታል።
20. እንዲህ ያለውን መባ ማቅረብ የማይችል ምስኪን ድኻ፣የማይነቅዝ ዕንጨት ይመርጣል፤የማይወድቅ ምስልን ለማቆምም፣ታዋቂ ባለ ሙያ ይፈልጋል።
21. አላወቃችሁምን?አልሰማችሁምን?ከጥንት አልተነገራችሁምን?ምድር ከተመሠረተች ጀምሮ አላስተዋላችሁምን?
22. እርሱ ከምድር ክበብ በላይ በዙፋን ላይ ይቀመጣል፤ሕዝቦቿም እንደ አንበጣ ናቸው።ሰማያትን እንደ ድባብ ይዘረጋቸዋል፤እንደ መኖሪያ ድንኳንም ይተክላቸዋል።