ኢሳይያስ 30:9-19 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

9. እነዚህም የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ለመስማት የማይፈልጉ፣ዐመፀኛ ሕዝቦችና አታላይ ልጆች ናቸው።

10. ባለ ራእዮችን፣“ከእንግዲህ ራእይን አትዩ” ይላሉ፤ነቢያትንም እንዲህ ይላሉ፤“እውነተኛውን ትንቢት ከእንግዲህ አትንገሩን፤ደስ የሚያሰኘውን ንገሩን፤የሚያማልለውን ተንብዩልን።

11. ከዚህ መንገድ ፈቀቅ በሉ፤ከጐዳናውም ራቁ፤ከእስራኤል ቅዱስ ጋርፊት ለፊት አታጋጥሙን።”

12. ስለዚህ፣ የእስራኤል ቅዱስ እንዲህ ይላል፤“ይህን ቃል ስላቃለላችሁ፣ግፍን ስለታመናችሁ፣ማታለልን ስለ ተደገፋችሁ፣

13. ስለዚህ ይህ ኀጢአት፣ተሰነጣጥቆ ሊወድቅ እንደ ደረሰ፣ሳይታሰብ ድንገት እንደሚወድቅ ረጅም ቅጥር ይሆንባችኋል።

14. ከስብርባሪዎቹም መካከል፣ለፍም መጫሪያ፣ለውሃ መጥለቂያ ገል እስከማይገኝ ድረስ፣ምንም ሳይቀር ክፉኛ እንደሚንኰታኰት፣የሸክላ ዕቃ ይደቃል።”

15. የእስራኤል ቅዱስ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“በመመለስና በማረፍ ትድናላችሁ፤በጸጥታና በመታመን ትበረታላችሁ፤እናንተ ግን ይህን አላደረጋችሁም፤

16. ደግሞም ‘አይሆንም፣ በፈረስ እንሸሻለን’ አላችሁ፤ስለዚህ ትሸሻላችሁ።ደግሞም፣ ‘በፈጣን ፈረስ እናመልጣለን’ አላችሁ፤ስለዚህ አሳዳጆቻችሁም ፈጣን ይሆናሉ።

17. በተራራ ዐናት ላይ እንደ ተተከለ ሰንደቅ ዐላማ፣በኰረብታም ላይ እንደ ቆመ ምልክት፣ሆናችሁ እስክትቀሩ ድረስበአንድ ሰው ዛቻ፣ሺህ ሰው ይሸሻል፤በአምስት ሰው፣ሁላችሁ ትሸሻላችሁ።”

18. እግዚአብሔር ግን ምሕረት ሊያደርግላችሁ ይታገሣል፤ርኅራኄም ሊያሳያችሁ ይነሣል። እግዚአብሔር የፍትሕ አምላክ ነውና፣እርሱን በመተማመን የሚጠባበቁት የተባረኩ ናቸው።

19. በኢየሩሳሌም የምትኖሩ የጽዮን ሕዝብ ሆይ፤ ከእንግዲህ ወዲህ አታለቅሱም። ለርዳታ ወደ እርሱ ስትጮኹ እንዴት ምሕረት አያደርግላችሁ ጩኸትህን እንደሰማም ፈጥኖ ይመልስልሃል።

ኢሳይያስ 30