ኢሳይያስ 30:17-28 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

17. በተራራ ዐናት ላይ እንደ ተተከለ ሰንደቅ ዐላማ፣በኰረብታም ላይ እንደ ቆመ ምልክት፣ሆናችሁ እስክትቀሩ ድረስበአንድ ሰው ዛቻ፣ሺህ ሰው ይሸሻል፤በአምስት ሰው፣ሁላችሁ ትሸሻላችሁ።”

18. እግዚአብሔር ግን ምሕረት ሊያደርግላችሁ ይታገሣል፤ርኅራኄም ሊያሳያችሁ ይነሣል። እግዚአብሔር የፍትሕ አምላክ ነውና፣እርሱን በመተማመን የሚጠባበቁት የተባረኩ ናቸው።

19. በኢየሩሳሌም የምትኖሩ የጽዮን ሕዝብ ሆይ፤ ከእንግዲህ ወዲህ አታለቅሱም። ለርዳታ ወደ እርሱ ስትጮኹ እንዴት ምሕረት አያደርግላችሁ ጩኸትህን እንደሰማም ፈጥኖ ይመልስልሃል።

20. ጌታ የጭንቀት እንጀራና የመከራ ውሃ ቢሰጥህም፣ አስተማሪህ ከእንግዲህ አይሰወርብህም፤ ዐይኖችህም አስተማሪህን ያያሉ።

21. ወደ ቀኝም ሆነ ወደ ግራ ዘወር ብትል ጆሮህ ከኋላህ፣ “መንገዱ ይህ ነው፤ በእርሱ ሂድ” የሚል ድምፅ ይሰማል።

22. ከዚያም በብር የተለበጡትን ጣዖቶችህንና በወርቅ የተለበዱ ምስሎችህን ታዋርዳለህ፤ “ከዚህ ወግ” ብለህም እንደ መርገም ጨርቅ ትጥላቸዋለህ።

23. በምድርም ለዘራኸው ዘር ዝናብን ይሰጥሃል፤ ከመሬትም የሚገኘው ፍሬ ምርጥና የተትረፈረፈ ይሆናል። በዚያን ቀን ከብቶችህ በትልቅ ሜዳ ላይ ይሰማራሉ።

24. የዕርሻ በሬዎችና አህዮች በመንሽና በላይዳ የተለየውን ገፈራና ድርቆሽ ይበላሉ።

25. በታላቁ የዕልቂት ቀን ምሽጎች ሲፈርሱ፣ በረጅም ተራራ ሁሉና ከፍ ባለውም ኰረብታ ሁሉ ላይ ወራጅ ወንዝ ይፈስሳል።

26. እግዚአብሔር የሕዝቡን ስብራት ሲጠግን፣ ያቈሰለውንም ሲፈውስ፣ ጨረቃ እንደ ፀሓይ ታበራለች፤ የፀሓይም ብርሃን እንደ ሰባት ቀን ብርሃን ሰባት ዕጥፍ ይደምቃል።

27. እነሆ፤ የእግዚአብሔር ስም፣ከሚነድ ቍጣ፣ ጥቅጥቅ ካለና ከሚትጐለጐል የጢስ ደመና ጋር ከሩቅ ይመጣል፤ከንፈሮቹ ቍጣን የተሞሉ ናቸው፤ምላሱም የሚባላ እሳት ነው።

28. እስትንፋሱ እንደሚጠራርግ፣እስከ ዐንገት እንደሚደርስም የውሃ ሙላት ነው፤መንግሥታትን በጥፋት ወንፊት ያበጥራቸዋል፤በሕዝቦችም መንጋጋ፣መንገድ የሚያስት ልጓም ያስገባል።

ኢሳይያስ 30