3. ምድር ፈጽሞ ባድማ ትሆናለች፤ጨርሶም ትበዘበዛለች፤ እግዚአብሔር ይህን ቃል ተናግሮአልና።
4. ምድር ትደርቃለች፤ ትረግፋለች፤ዓለም ትዝላለች፤ ትረግፋለች፤የምድርም መሳፍንት ይዝላሉ።
5. ምድር በሕዝቧ ትረክሳለች፤ሕግን ጥሰዋል፤ሥርዐትን ተላልፈዋል፤ዘላለማዊውንም ኪዳን አፍርሰዋል።
6. ስለዚህ ርግማን ምድርን ትበላለች፤ሕዝቦቿም ስለ በደላቸው ይቀጣሉ፤ስለዚህ የምድር ነዋሪዎች ተቃጥለዋል፤በጣም ጥቂት የሆኑት ቀርተዋል።
7. አዲሱ የወይን ጠጅ አለቀ፤ የወይኑም ተክል ደረቀ፤ደስተኞችም ሁሉ አቃሰቱ።
8. የከበሮ ደስታ ጸጥ አለ፤የጨፋሪዎች ጩኸት አበቃ፤ደስ የሚያሰኘውም በገና እረጭ አለ።
9. ከእንግዲህ እየዘፈኑ የወይን ጠጅ አይጠጡም፤መጠጡም ለሚጠጡት ይመራል።
10. የፈራረሰችው ከተማ ባድማ ሆነች፤የየቤቱም መግቢያ ተዘጋ።
11. በየአደባባዩ የወይን ጠጅ ያለህ እያሉ ይጮኻሉ፤ደስታው ሁሉ ወደ ሐዘን ይለወጣል፤ሐሤቱም ሁሉ ከምድር ገጽ ጠፍቶአል።