22. የሚያከብሩበትም ምክንያት አይሁድ ከጠላቶቻቸው ዕረፍት ያገኙበት፣ ሐዘናቸው ወደ ደስታ፣ ልቅሷቸውም ወደ ክብረ በዓል የተለወጠበት ቀን ስለ ሆነ ነው። ቀኖቹንም የተድላና የደስታ ቀኖች አድርገው፣ እርስ በርሳቸውም የምግብ ስጦታ እየተለዋወጡና ለድኾችም ስጦታ እየሰጡ እንዲያከብሩ ጻፈላቸው።
23. ስለዚህ አይሁድ መርዶክዮስ የጻፈላቸውን ለመፈጸምና የጀመሩትን በዓል ለማክበር ተስማሙ፤
24. ምክንያቱም የአይሁድ ሁሉ ጠላት የሆነው የአጋጋዊው የሐመዳቱ ልጅ ሐማ አይሁድን ለማጥፋት አሢሮ ነበር፤ ሊፈጃቸውና ሊያጠፋቸውም ፉር የተባለ ዕጣ ጥሎ ነበር።
25. ሤራው በንጉሡ ዘንድ እንደ ታወቀ ሐማ በአይሁድ ላይ የሸረበው ሤራ በገዛ ራሱ ላይ እንዲጠመጠም፣ እርሱና ወንዶች ልጆቹም በዕንጨት ላይ እንዲሰቀሉ የጽሑፍ ትእዛዝ አስተላለፈ።