10. መርዶክዮስ ትእዛዙን በንጉሥ ጠረክሲስ ስም ጽፎ በንጉሡ የቀለበት ማኅተም አተመው፤ ከዚያም በተለይ ለንጉሡ በተገሩ ፈጣን ፈረሶች በሚጋልቡ መልእክተኞች እጅ ላከው።
11. የንጉሡም ዐዋጅ በየከተማው የሚኖሩ አይሁድ ሁሉ እንዲሰበሰቡና ራሳቸውን ከጥቃት እንዲከላከሉ እንዲሁም በራሳቸው፣ በሚስቶቻቸውና በልጆቻቸው ላይ አደጋ የሚያደርስባቸውን የየትኛውንም ዜጋ ወይም አውራጃ የታጠቀ ኀይል እንዲያጠፉ፣ እንዲገድሉ፣ እንዲደመስሱና የጠላቶቻቸውን ሀብት እንዲዘርፉ ፈቀደላቸው።
12. አይሁድ በመላው የንጉሥ ጠረክሲስ አውራጃ ሁሉ ይህን እንዲፈጽሙ የተወሰነው አዳር በተባለው በዐሥራ ሁለተኛው ወር ዐሥራ ሦስተኛ ቀን ነበር።
13. አይሁድ በዚያን ቀን ጠላቶቻቸውን ለመበቀል ዝግጁ እንዲሆኑ፣ የዋናው ዐዋጅ ቅጅ ሕግ ወደየአውራጃው እንዲላክና የየአገሩም ሕዝብ እንዲያውቀው ተደረገ።
14. በቤተ መንግሥቱ ፈረሶች የተቀመጡ መልእክተኞችም፣ በንጉሡ አስቸኳይ ትእዛዝ ጋልበው ወጡ፤ ዐዋጁም በሱሳ ግንብ ተነገረ።
15. መርዶክዮስ ሰማያዊና ነጭ የቤተ መንግሥት ልብስ ለብሶ፣ ትልቅ የወርቅ አክሊል ደፍቶ፣ ከቀጭን በፍታና ከሐምራዊ ግምጃ የተሠራ መጐናጸፊያ ተጐናጽፎ ከንጉሡ ፊት ወጣ፤ የሱሳ ከተማም ደስታ የተሞላበት በዓል አከበረች።
16. ጊዜውም ለአይሁድ የደስታና የፈንጠዝያ፣ የተድላና የክብር ወቅት ሆነላቸው።
17. የንጉሡ ዐዋጅ በደረሰበት በእያንዳንዱ አውራጃና በእያንዳንዱ ከተማ አይሁድ ደስ አላቸው፤ ሐሤት አደረጉ፤ የፈንጠዝያና የደስታም ቀን ሆነላቸው። አይሁድን ከመፍራታቸው የተነሣ፣ ከሌሎች አገር ዜጎች ብዙ ሕዝብ አይሁድ ሆኑ።