1. ከህንድ ጀምሮ እስከ ኢትዮጵያ ድረስ ያሉትን አንድ መቶ ሃያ ሰባት አገሮች ይገዛ በነበረው በጠረክሲስ ዘመነ መንግሥት እንዲህ ሆነ፤
2. በዚያን ዘመን ንጉሡ ጠረክሲስ የገዛው በሱሳ ግንብ ባለው ንጉሣዊ ዙፋኑ ሆኖ ነበር።
3. እርሱም በነገሠ በሦስተኛው ዓመት ለመኳንንቱና ለሹማምቱ ሁሉ ታላቅ ግብዣ አደረገ። በግብዣውም የፋርስና የሜዶን የጦር አዛዦች፣ መሳፍንትና የየአውራጃው መኳንንት ተገኝተው ነበር።
4. ለእነርሱም የመንግሥቱን ሰፊ ሀብት፣ የግርማውን ታላቅነትና ክብር አንድ መቶ ሰማንያ ቀን ሙሉ አሳያቸው።
5. እነዚህ ቀናት ካለፉ በኋላ፣ ንጉሡ በሱሳ ግንብ ለነበሩት፣ ከትንሽ እስከ ትልቅ ላለው ሕዝብ ሁሉ፣ በቤተ መንግሥቱ ውስጥ ዙሪያውን በአትክልት በተከበበው አደባባይ ሰባት ቀን የፈጀ ግብዣ አደረገ።