ነህምያ 4:4-11 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

4. አምላካችን ሆይ፤ ተንቀናልና ስማን፤ ስድባቸውን በራሳቸው ላይ አውርድባቸው፤ በምርኮ ምድር እንዲበዘበዙ አሳልፈህ ስጣቸው።

5. የፈረሰውን በሚሠሩት ፊት የስድብ ናዳ አውርደዋልና በደላቸውን ይቅር አትበል፤ ኀጢአታቸውንም ከፊትህ አታጥፋው።

6. ሕዝቡ ከልቡ ስለሚሠራ፣ ቅጥሩን እኩሌታው ድረስ መልሰን ሠራነው።

7. ሰንባላጥ፣ ጦቢያ፣ ዐረቦች፣ የአሞንና የአሽዶድ ሰዎች፣ የኢየሩሳሌም ቅጥር ሥራ እየተፋጠነና ክፍት ቦታዎቹም ሁሉ እየተሞሉ መሆናቸውን በሰሙ ጊዜ እጅግ ተቈጡ።

8. መጥተውም ኢየሩሳሌምን ይወጉ ዘንድ፣ ሽብርንም ይፈጥሩ ዘንድ ሁሉም በአንድነት አደሙ።

9. እኛ ግን ወደ እግዚአብሔር ጸለይን፤ ዛቻቸውንም ለመቋቋም ቀንና ሌሊት የሚጠብቁ ዘቦችን መደብን።

10. በዚህ ጊዜ የይሁዳ ሕዝብ፣ “የሠራተኞቹ ጒልበት እየደከመ ነው፤ ከፍርስራሹም ብዛት የተነሣ ቅጥሩን መልሰን ለመሥራት አንችልም” አሉ።

11. ጠላቶቻችን ደግሞ፣ “በመካከላቸው ገብተን እስክንገድላቸውና ሥራውን እስክናስቆም ድረስ አያውቁም ወይም አያዩም” አሉ።

ነህምያ 4