27. ከእነርሱ ቀጥሎ የቴቁሐ ሰዎች ከታላቁ ግንብ ትይዩ ጀምሮ እስከ ዖፌል ቅጥር ድረስ ያለውን ሌላ ክፍል መልሰው ሠሩ።
28. “የፈረስ በር” ተብሎ ከሚጠራው በላይ ያለውን ደግሞ ካህናቱ እያንዳንዳቸው በየመኖሪያ ቤታቸው ትይዩ ያለውን መልሰው ሠሩ።
29. ከእነርሱም ቀጥሎ የኢሜር ልጅ ሳዶቅ በቤቱ ትይዩ ያለውን መልሶ ሠራ። ከእርሱ ቀጥሎ ያለውን “የምሥራቅ በር” ጠባቂ የሆነው የሴኬንያ ልጅ ሸማያ መልሶ ሠራ።
30. ከእርሱ ቀጥሎ ያለውን ሌላ ክፍል ደግሞ የሰሌምያ ልጅ ሐናንያና የሴሌፍ ስድስተኛ ልጅ ሐኖን መልሰው ሠሩ። ከእነርሱም ቀጥሎ የበራክያ ልጅ ሜሱላም ከመኖሪያው ትይዩ ያለውን መልሶ ሠራ።