ነህምያ 3:19-32 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

19. ከእርሱም ቀጥሎ ወደ ጦር መሣሪያ ግምጃ ቤት በሚያወጣውና እስከ ማእዘኑ በሚደርሰው ትይዩ ያለውን ሌላ ክፍል የምጽጳ ገዥ የኢያሱ ልጅ ኤጽር መልሶ ሠራ።

20. ከእርሱም ቀጥሎ የዘባይ ልጅ ባሮክ ከማእዘኑ ጀምሮ እስከ ሊቀ ካህኑ እስከ ኤልያሴብ ቤት መግቢያ ያለውን ሌላ ክፍል በትጋት መልሶ ሠራ።

21. ከእርሱ ቀጥሎ ከኤልያሴብ ቤት መግቢያ ጀምሮ እስከ መጨረሻው ያለውን ሌላ ክፍል የአቆስ ልጅ የኦርዮ ልጅ ሜሪሞት መልሶ ሠራ።

22. ከእርሱም ቀጥሎ ያለውን ክፍል ከአካባቢው የመጡት ካህናት መልሰው ሠሩ።

23. ከእነርሱ ቀጥሎ ብንያምና አሱብ ከቤታቸው ፊት ለፊት ያለውን መልሰው ሠሩ፤ ከእነርሱም ቀጥሎ የሐናንያ ልጅ የመዕሤያ ልጅ ዓዛርያስ በቤቱ አጠገብ ያለውን መልሶ ሠራ።

24. ከእርሱም ቀጥሎ ከዓዛርያስ ቤት ጀምሮ እስከ ማዕዘኑና እስከ ማዕዘኑም ጫፍ ያለውን ሌላውን ክፍል የኤንሐደድ ልጅ ቢንዊ መልሶ ሠራ፤

25. የኡዛይ ልጅ ፋላል ከቅጥሩ ማእዘን ትይዩና በዘብ መጠበቂያው አደባባይ አጠገብ ካለው ከላይኛው ቤተ መንግሥት መጠበቂያ ግንብ ጀምሮ ያለውን መልሶ ሠራ። ከእርሱም ቀጥሎ የፋሮስ ልጅ ፈዳያና

26. በዖፌል ኰረብታ ላይ የሚኖሩት የቤተ መቅደሱ አገልጋዮች “የውሃ በር” ተብሎ ከሚጠራው ትይዩ ጀምሮ በስተ ምሥራቅ እስከሚገኘው ግንብ ድረስ መልሰው ሠሩ።

27. ከእነርሱ ቀጥሎ የቴቁሐ ሰዎች ከታላቁ ግንብ ትይዩ ጀምሮ እስከ ዖፌል ቅጥር ድረስ ያለውን ሌላ ክፍል መልሰው ሠሩ።

28. “የፈረስ በር” ተብሎ ከሚጠራው በላይ ያለውን ደግሞ ካህናቱ እያንዳንዳቸው በየመኖሪያ ቤታቸው ትይዩ ያለውን መልሰው ሠሩ።

29. ከእነርሱም ቀጥሎ የኢሜር ልጅ ሳዶቅ በቤቱ ትይዩ ያለውን መልሶ ሠራ። ከእርሱ ቀጥሎ ያለውን “የምሥራቅ በር” ጠባቂ የሆነው የሴኬንያ ልጅ ሸማያ መልሶ ሠራ።

30. ከእርሱ ቀጥሎ ያለውን ሌላ ክፍል ደግሞ የሰሌምያ ልጅ ሐናንያና የሴሌፍ ስድስተኛ ልጅ ሐኖን መልሰው ሠሩ። ከእነርሱም ቀጥሎ የበራክያ ልጅ ሜሱላም ከመኖሪያው ትይዩ ያለውን መልሶ ሠራ።

31. ከእርሱ ቀጥሎ ከወርቅ አንጥረኞች አንዱ መልክያ በመቈጣጠሪያው በር ትይዩ እስከሚገኘው እስከ ቤተ መቅደሱ አገልጋዮችና እስከ ነጋዴዎቹ ቤት፣ እንዲሁም ከማእዘኑ በላይ እስከሚገኘው ክፍል ያለውን መልሶ ሠራ፤

32. ከማእዘኑ በላይ ከሚገኘው ክፍል ጀምሮ እስከ በጎች በር ያለውን ደግሞ ወርቅ አንጥረኞቹና ነጋዴዎቹ መልሰው ሠሩ።

ነህምያ 3