ነህምያ 3:1-20 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ሊቀ ካህናቱ ኤልያሴብና ወንድሞቹ ካህናት ለሥራ ተነሡ፤ የበጎች በር የተባለውንም እንደ ገና ሠሩ። ቀደሱት፤ መዝጊያዎቹንም በየቦታቸው ላይ አቆሙ። መቶ ማማ እስከሚባለው ግንብና ሐናንኤል ማማ ተብሎ እስከሚጠራው ድረስ ሠርተው ቀደሱት፤

2. ቀጥሎ ያለውንም የኢያሪኮ ሰዎች ሠሩ፤ እነርሱ ከሠሩት ቀጥሎ ደግሞ የአምሪ ልጅ ዘኩር ሠራ።

3. የዓሣ በሩን የሃስናአ ልጆች ሠሩ፤ እነርሱም ምሰሶዎቹን አቁመው መዝጊያዎቹን፣ መቀርቀሪያዎቹንና መወርወሪያዎቹን በየቦታቸው አኖሩ።

4. የአቆስ ልጅ የኦርዮ ልጅ ሜሪሞት ከዚያቀጥሎ ያለውን ክፍል መልሶ ሠራ። ከእርሱ ቀጥሎ ያለውን የሜሴዜቤል ልጅ የበራክያ ልጅ ሜሱላም መልሶ ሠራ። ከእርሱ ቀጥሎ ያለውን የበዓና ልጅ ሳዶቅ መልሶ ሠራ፤

5. የሚቀጥለውን ክፍል የቴቁሐ ሰዎች መልሰው ሠሩ፤ መኳንንቶቻቸው ግን በተቈጣ ጣሪ አሠሪዎቻቸው ሥር ሆነው በሥራው መጠመድ አልፈለጉም።

6. አሮጌውን በር የፋሴሐ ልጅ ዮዳሄና የበሶድያ ልጅ ሜሱላም መልሰው ሠሩ፤ እነርሱም ምሰሶዎቹን አቁመው መዝጊያዎቹን፣ ማያያዣዎቹንና መወርወሪያዎቹን በየቦታቸው አኖሩ።

7. ከእነርሱም ቀጥሎ የዕድሳቱ ሥራ የተከናወነው በኤፍራጥስ ማዶ በሚገኘው አገረ ገዥ ሥልጣን ሥር ባሉት በገባዖንና በምጽጳ ሰዎች በገባዖናዊው በመልጥያና በሜሮኖታዊው በያዶን ነበር።

8. ከወርቅ አንጥረኞች አንዱ የሆነው የሐር ሃያ ልጅ ዑዝኤል የሚቀጥለውን ክፍል ሠራ፤ ከሽቱ ቀማሚዎች አንዱ የሆነው ሐናንያ ደግሞ ከዚያቀጥሎ ያለውን መልሶ ሠራ። እነርሱም “ሰፊው ቅጥር” ተብሎ እስከሚጠራው ድረስ ኢየሩሳሌምን መልሰው ሠሩ።

9. ከዚያ የሚቀጥለውን ክፍል የኢየሩሳሌም አውራጃ እኩሌታ ገዥ የሆነው የሆር ልጅ ረፋያ መልሶ ሠራ።

10. የኤርማፍ ልጅ ይዳያ ከቤቱ ፊት ለፊት ያለውን ክፍል መልሶ ሠራ፤ የአሰበንያ ልጅ ሐጡስ ደግሞ ከእርሱ ቀጥሎ ያለውን መልሶ ሠራ።

11. የካሪም ልጅ መልክያና የፈሐት ሞዓብ ልጅ አሱብ ሌላውን ክፍልና “የእቶን ግንብ” ተብሎ የሚጠራውን መልሰው ሠሩ።

12. የኢየሩሳሌም አውራጃ እኩሌታ ገዥ የሆነው የአሎኤስ ልጅ ሰሎም ከሴት ልጆቹ ጋር በመሆን ቀጥሎ ያለውን ክፍል መልሶ ሠራ።

13. “የሸለቆ በር” ተብሎ የሚጠራውን የሐኖንና የዛኖ ነዋሪዎች ዐደሱት፤ መልሰው ሠሩት፤ ከሠሩትም በኋላ መዝጊያዎቹን በየቦታቸው አኖሩ፤ መወርወሪያዎቹንና መቀርቀሪያዎቹንም አበጁ። እንዲሁም “የቆሻሻ መጣያ በር” ተብሎ እስከሚጠራው ድረስ ያለውን አንድ ሺህ ክንድ ቅጥር መልሰው ሠሩ።

14. “የቈሻሻ መጣያ በር” ተብሎ የሚጠራው የቤት ሐካሪም አውራጃ ገዥ የሆነው የሬካብ ልጅ መልክያ መልሶ ሠራ፤ መልሶ ከሠራ በኋላም መዝጊያዎቹን፣ መቀርቀሪያዎቹንና መወርወሪያዎቹን በየቦታቸው አኖረ።

15. የምጽጳ አውራጃ የኮልሖዜ ልጅ ሰሎም “የምንጭ በር” ተብሎ የሚጠራውን መልሶ ሠራ፤ መልሶ ከሠራም በኋላ ከድኖ መዝጊያዎቹን በየቦታቸው አኖረ፤ መወርወሪያዎቹንና መቀርቀሪያዎቹንም አበጀ። “የንጉሥ አትክልት ቦታ” ተብሎ በሚጠራው አጠገብ የሚገኘውን የሼላን መዋኛ ግንብም፣ ከዳዊት ከተማ ጀምሮ ቍልቍል እስከሚወርደው ደረጃ ድረስ መልሶ ሠራ።

16. ከእርሱም በኋላ የቤት ጹር አውራጃ እኩሌታ ገዥ የዓዝቡቅ ልጅ ነህምያ እስከ ዳዊት መቃብር ትይዩ እስከ ሰው ሠራሹ ኵሬና “የጀግኖች ቤት” ተብሎ እስከሚጠራው ድረስ ያለውን መልሶ ሠራ።

17. ከእርሱ ቀጥሎ ሌዋውያኑ በባኒ ልጅ በሬሁ ሥር ሆነው የዕድሳት ሥራ ሠሩ። ከእርሱ ቀጥሎ የቅዒላ አውራጃ እኩሌታ ገዥ ሐሸብያ አውራጃውን መልሶ ሠራ።

18. ከእርሱ ቀጥሎ ያለውን ክፍል ደግሞ የሌላው የቅዒላ አውራጃ እኩሌታ ገዥ የኤንሐዳድ ልጅ በዋይና በእርሱም ሥር የነበሩት የአገሩ ሰዎች መልሰው ሠሩ።

19. ከእርሱም ቀጥሎ ወደ ጦር መሣሪያ ግምጃ ቤት በሚያወጣውና እስከ ማእዘኑ በሚደርሰው ትይዩ ያለውን ሌላ ክፍል የምጽጳ ገዥ የኢያሱ ልጅ ኤጽር መልሶ ሠራ።

20. ከእርሱም ቀጥሎ የዘባይ ልጅ ባሮክ ከማእዘኑ ጀምሮ እስከ ሊቀ ካህኑ እስከ ኤልያሴብ ቤት መግቢያ ያለውን ሌላ ክፍል በትጋት መልሶ ሠራ።

ነህምያ 3