ነህምያ 11:18-35 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

18. በቅድስቲቱ ከተማ ውስጥ የነበሩት የሌዋውያኑ ቍጥር 284 ነበረ።

19. በር ጠባቂዎች፦ዓቁብ፣ ጤልሞንና በሮቹን የሚጠብቁ ወንድሞቻቸው፣ 172 ሰዎች።

20. የቀሩት እስራኤላውያንም ከካህናቱና ከሌዋውያኑ ጋር በይሁዳ ከተሞች ሁሉ በየርስታቸው ተቀመጡ።

21. የቤተ መቅደሱ አገልጋዮች በዖፌል ኰረብታ ላይ ተቀመጡ፤ ሲሐና ጊሽጳ በእነርሱ ላይ ያዙ ነበር።

22. በኢየሩሳሌም የሌዋውያኑ ዋና አለቃ የሚካ ልጅ፣ የመታንያ ልጅ፣ የሐሻብያ ልጅ፣ የባኒ ልጅ ኦዚ ነበረ፤ ኦዚ በእግዚአብሔር ቤት አገልግሎት ለሚዘመረው መዝሙር ኀላፊ ከነበሩት ከአሳፍ ዘሮች አንዱ ነበረ።

23. መዘምራኑ የየዕለቱን ተግባራቸውን በሚቈጣጠረው በንጉሡ ትእዛዝ ሥር ነበሩ።

24. የይሁዳ ልጅ የዛራ ዘር የሆነው የሜሴዜቤል ልጅ ፈታያ ሕዝቡን በሚመለከት ጒዳይ ሁሉ የንጉሡ ተወካይ ነበር።

25. ከይሁዳ ሕዝብ ጥቂቱ በመንደሮችና በእርሻ ቦታዎች፣ በቂርያት አርባቅና በዙሪያዋ ባሉ መኖሪያዎቿ፣ በዲቦንና በመኖሪያዎቿ፣ በይቀብጽኤልና በመንደሮቿ ተቀመጡ፤

26. በኢያሱ፣ በሞላዳ፣ በቤትጳሌጥ፣

27. በሐጸርሹዓል፣ በቤርሳቤህና በመኖሪያዎቿ፣

28. በጺቅላግ፣ በምኮናና በመኖሪያዎቿ፣

29. በዓይንሪሞን፣ በጾርዓ፣ በየርሙት፣

30. በዛኖዋ፣ በዓዶላምና በመንደሮቻቸው፣ በለኪሶና በእርሻዎቿ፣ በዓዜቃና በመንደሮቿ። ስለዚህ ከቤርሳቤህ ጀምሮ እስከ ሄኖም ሸለቆ ባለው ስፍራ ሁሉ ተቀመጡ።

31. ከጌባ የመጡት የብንያም ዘሮች በማክማስ፣ በጋያ፣ በቤቴልና በመኖሪያዎቿ፣

32. በዓናቶት፣ በኖብና በሐናንያ፣

33. በሐጾር፣ በራማና በጊቴም፣

34. በሐዲድ፣ በስቦይምና በንበላት፣

35. በሎድና በኦኖ፣ ደግሞም “የእጅ ጥበብ ባለ ሙያዎች ሸለቆ” በተባለው ስፍራ ተቀመጡ።

ነህምያ 11