5. ብርታትንና መጽናናትን የሚሰጥ አምላክ፣ ክርስቶስ ኢየሱስን ስትከተሉ፣ በመካከላችሁ የአንድነትን መንፈስ ይስጣችሁ፤
6. ይኸውም በአንድ ልብና በአንድ አፍ ሆናችሁ፣ የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክና አባት ታከብሩ ዘንድ ነው።
7. እንግዲህ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሆን ዘንድ ክርስቶስ እንደተቀበላችሁ፣ እርስ በርሳችሁ ተቀባበሉ።
8. ለአባቶች የተሰጠውን የተስፋ ቃል ያጸና ዘንድ ለእግዚአብሔር እውነት ሲል ክርስቶስ የአይሁድ አገልጋይ እንደሆነ እነግራችኋለሁና፤
9. እንዲሁም አሕዛብ እግዚአብሔርን ስለ ምሕረቱ ያመሰግኑት ዘንድ ነው፤ እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፤“ስለዚህ በአሕዛብ መካከል አመሰግንሃለሁ፤ለስምህም እዘምራለሁ።”
10. ደግሞም፣“አሕዛብ ሆይ፤ ከሕዝቡ ጋር ደስ ይበላችሁ” ይላል።
11. እንደ ገናም፣“አሕዛብም ሁላችሁ ጌታን አመስግኑ፤ሕዝቦች ሁሉ ወድሱት” ይላል።
12. ኢሳይያስም እንዲሁ፣“በሕዝቦች ሁሉ ላይ የሚነግሠው፣የእሴይ ሥር ይመጣል፤በእርሱም አሕዛብ ተስፋ ያደርጋሉ” ይላል።
13. በእርሱ በመታመናችሁ የተስፋ አምላክ ደስታንና ሰላምን ሁሉ ይሙላባችሁ፤ ይኸውም በመንፈስ ቅዱስ ኀይል ተስፋ ተትረፍርፎ እንዲፈስላችሁ ነው።
14. ወንድሞቼ ሆይ፤ እናንተ ራሳችሁ በበጎነት የተሞላችሁ፣ በዕውቀት ሁሉ እንደ ተሞላችሁና አንዱ ሌላውን ለመምከር ችሎታ ያላችሁ መሆናችሁን እኔ ራሴ ርግጠኛ ሆኜ አለሁ።
15. እግዚአብሔር በሰጠኝ ጸጋ መሠረት፣ እንደ ገና ዐሳስባችሁ ዘንድ በአንዳንድ ጒዳዮች ላይ በድፍረት የጻፍሁላችሁ፣
16. በእግዚአብሔር ወንጌል የክህነት ተግባር፣ ለአሕዛብ የክርስቶስ ኢየሱስ አገልጋይ ለመሆን ነው፤ ይኸውም አሕዛብ በመንፈስ ቅዱስ ተቀድሰው በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ያለው መሥዋዕት እንዲሆኑ ነው።