ሮሜ 14:6-13 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

6. አንድን ቀን ከሌላው የተለየ አድርጎ የሚያስብ ሰው፣ እንዲህ የሚያደርገው ለጌታ ብሎ ነው፤ ሥጋ የሚበላውም ለጌታ ብሎ ይበላል፤ ለእግዚአብሔር ምስጋና ያቀርባልና። የማይበላም ለጌታ ሲል አይበላም፤ ለእግዚአብሔርም ምስጋና ያቀርባል።

7. ከእኛ ማንም ለራሱ የሚኖር፣ ለራሱም የሚሞት የለምና።

8. ብንኖር ለጌታ እንኖራለን፤ ብንሞትም ለጌታ እንሞታለን፤ ስለዚህ ብንኖርም ብንሞትም የጌታ ነን።

9. ለዚሁ፣ የሙታንና የሕያዋን ጌታ ይሆን ዘንድ ክርስቶስ ሞቶአል፤ በሕይወትም ተነሥቶአል።

10. ታዲያ አንተ በወንድምህ ላይ ለምን ትፈርዳለህ? ለምንስ ወንድምህን ትንቃለህ? ሁላችንም በእግዚአብሔር የፍርድ ወንበር ፊት እንቀርባለንና፤

11. እንዲህ ተብሎ ተጽፎአል፤“ ‘እኔ ሕያው ነኝና’፤‘ጒልበት ሁሉ ለእኔ ይንበረከካል፤ምላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር ይመሰክራል’ ” ይላል ጌታ።

12. ስለዚህ እያንዳንዳችን ስለ ራሳችን ለእግዚአብሔር መልስ እንሰጣለን።

13. ስለዚህ እርስ በርሳችን፣ አንዱ በሌላው ላይ ከመፍረድ እንቈጠብ፤ በዚህ ፈንታ ግን በወንድምህ መንገድ ላይ የማሰናከያ ድንጋይ ወይም ወጥመድ እንዳታስቀምጥ ቊርጥ ሐሳብ አድርግ።

ሮሜ 14