ሮሜ 12:10-21 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

10. እርስ በርሳችሁ በወንድማማች መዋደድ አጥብቃችሁ ተዋደዱ፤ አንዱ ሌላውን ከራሱ በማስበለጥ እርስ በርሳችሁ ተከባበሩ።

11. ጌታን ለማገልገል በመንፈስ የጋላችሁ ሁኑ እንጂ ከዚህ ትጋት ወደ ኋላ አትበሉ።

12. በተስፋ ደስተኞች ሁኑ፤ በመከራ ታገሡ፤ በጸሎት ጽኑ።

13. ችግረኛ ለሆኑ ቅዱሳን ካላችሁ አካፍሉ፤ እንግዶችን ተቀበሉ።

14. የሚያሳድዷችሁን መርቁ፤ መርቁ እንጂ አትርገሙ።

15. ደስ ከሚላቸው ጋር ደስ ይበላችሁ፤ ከሚያዝኑም ጋር እዘኑ።

16. እርስ በርሳችሁ በመስማማት ኑሩ። ዝቅተኛ ኑሮ ውስጥ ካሉ ጋር አብራችሁ ለመሆን ፍቀዱ እንጂ አትኵራሩ፤ በራሳችሁም አትመኩ።

17. ለማንም ክፉን በክፉ አትመልሱ፤ በሰው ሁሉ ፊት በጎ የሆነውን ነገር ለማድረግ ትጉ።

18. ቢቻላችሁስ በበኩላችሁ ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ።

19. ወዳጆቼ ሆይ፤ ለእግዚአብሔር ቊጣ ፈንታ ስጡ እንጂ አትበቀሉ፤ “በቀል የእኔ ነው፤ እኔ ብድራትን እመልሳለሁ” ይላል ጌታ ተብሎ ተጽፎአልና።

20. ይልቁንስ፣“ጠላትህ ቢራብ አብላው፤ቢጠማም አጠጣው።ይህን በማድረግህም የእሳት ፍም በራሱ ላይ ትከምራለህ።”

21. ክፉን በመልካም አሸንፍ እንጂ በክፉ አትሸነፍ።

ሮሜ 12