ራእይ 9:9-18 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

9. የብረት ጥሩር የሚመስል ጥሩር ነበራቸው፤ የክንፎቻቸውም ድምፅ ወደ ጦርነት የሚገሠግሡ የብዙ ፈረሶችና ሠረገሎች ድምፅ ይመስል ነበር።

10. እንደ ጊንጥም ያለ ጅራትና መንደፊያ ነበራቸው፤ ደግሞም ሰዎችን አምስት ወር የሚያሠቃዩበት ኀይል በጅራታቸው ላይ ነበር።

11. በላያቸው ንጉሥ ነበራቸው፤ እርሱም የጥልቁ ጒድጓድ መልአክ ነው፤ ስሙም በዕብራይስጥ “አብዶን”፣ በግሪክ ደግሞ “አጶልዮን” ይባላል።

12. የመጀመሪያው ወዮ ዐልፎአል፤ እነሆ፤ ከዚህ በኋላ ገና ሌላ ሁለት ወዮዎች ይመጣሉ።

13. ስድስተኛው መልአክ መለከቱን ነፋ፤ በእግዚአብሔር ፊት ካለው በወርቅ ከተሠራው መሠዊያ ቀንዶች ድምፅ ሲመጣ ሰማሁ፤

14. ድምፁም መለከት የያዘውን ስድስተኛውን መልአክ፣ “በታላቁ ወንዝ በኤፍራጥስ የታሰሩትን አራቱን መላእክት ፍታቸው” አለው።

15. ከሰው ዘር አንድ ሦስተኛውን እንዲገድሉ፣ ለዚህች ሰዓትና ዕለት እንዲሁም ለዚህች ወርና ዓመት ተዘጋጅተው የነበሩት አራቱ መላእክት ተፈቱ።

16. የፈረሰኛው ሰራዊት ብዛት ሁለት መቶ ሚሊዮን ነበር፤ ቊጥራቸውንም ሰማሁ።

17. በራእዬ ያየኋቸው ፈረሶችና በላያቸውም የተቀመጡት ይህን ይመስሉ ነበር፤ ጥሩራቸው እንደ እሳት ቀይ፣ እንደ ያክንት ሰማያዊና እንደ ዲን ብጫ ነበር፤ የፈረሶቹ ራስ የአንበሶችን ራስ ይመስል ነበር። ከአፋቸውም እሳትና ጢስ፣ ዲንም ይወጣ ነበር።

18. ከአፋቸው በወጡት፣ በሦስቱ መቅሠፍቶች፣ ማለት በእሳቱ፣ በጢሱና በዲኑ አንድ ሦስተኛው የሰው ዘር ተገደለ።

ራእይ 9