ራእይ 22:2-16 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

2. ወንዙም በከተማዪቱ አውራ መንገድ መካከል ይፈስ ነበር። በወንዙ ግራና ቀኝ በየወሩ እያፈራ ዐሥራ ሁለት ጊዜ ፍሬ የሚሰጥ የሕይወት ዛፍ ነበረ፤ የዛፉም ቅጠሎች ሕዝቦች የሚፈወሱባቸው ነበሩ።

3. ከእንግዲህ ወዲህ ርግማን ከቶ አይኖርም፤ የእግዚአብሔርና የበጉ ዙፋን በከተማዪቱ ውስጥ ይሆናል፤ አገልጋዮቹም ያመልኩታል፤

4. ፊቱን ያያሉ፤ ስሙም በግምባራቸው ላይ ይሆናል።

5. ከእንግዲህ ወዲህ ሌሊት አይኖርም፤ ጌታ አምላክ ስለሚያበራላቸው የመብራት ወይም የፀሓይ ብርሃን አያስፈልጋቸውም፤ ከዘላለም እስከ ዘላለም ይነግሣሉ።

6. መልአኩም፣ “እነዚህ ቃሎች የታመኑና እውነተኞች ናቸው። የነቢያት መናፍስት ጌታ አምላክ በቅርብ የሚሆነውን ነገር ለአገልጋዮቹ እንዲያሳይ መልአኩን ልኮአል” አለኝ።

7. “እነሆ፤ ቶሎ እመጣለሁ፤ የዚህን መጽሐፍ የትንቢት ቃል የሚጠብቅ ብፁዕ ነው።”

8. እነዚህን ነገሮች የሰማሁና ያየሁ እኔ ዮሐንስ ነኝ። እነዚህን ነገሮች በሰማሁና ባየሁ ጊዜ፣ እነዚህን ነገሮች ላሳየኝ መልአክ ልሰግድ በእግሩ ሥር ተደፋሁ፤

9. እርሱ ግን፣ “ተው፤ ይህን አታድርግ እኔ ከአንተና ከወንድሞችህ ከነቢያት እንዲሁም የዚህን መጽሐፍ ቃል ከሚጠብቁት ሁሉ ጋር አገልጋይ ነኝ፤ ለእግዚአብሔር ስገድ” አለኝ።

10. እንዲህም አለኝ፤ “ጊዜው ስለ ደረሰ፣ የዚህን መጽሐፍ የትንቢት ቃል በማኅተም አትዝጋው፤

11. ዐመፀኛው በዐመፁ ይቀጥል፤ ርኩሱም ይርከስ፤ ጻድቁም ይጽደቅ፤ ቅዱሱም ይቀደስ።”

12. “እነሆ፤ ቶሎ እመጣለሁ፤ ዋጋዬ በእኔ ዘንድ አለ፤ ለእያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን እከፍለዋለሁ።

13. አልፋና ዖሜጋ፣ ፊተኛውና ኋለኛው፣ መጀመሪያውና መጨረሻው እኔ ነኝ።

14. “ወደ ሕይወት ዛፍ ለመድረስና በበሮቿም በኩል ወደ ከተማዪቱ ለመግባት መብት እንዲኖራቸው ልብሳቸውን የሚያጥቡ ብፁዓን ናቸው።

15. ውሾች፣ አስማተኞች፣ ሴሰኞች፣ ነፍሰ ገዳዮች፣ ጣዖት አምላኪዎች፣ ውሸትን የሚወዱና የሚያደርጉ ሁሉ በውጭ አሉ።

16. “እኔ ኢየሱስ እነዚህን ነገሮች እንዲመሰክር መልአኬን ለአብያተ ክርስቲያናት ልኬአለሁ። እኔ የዳዊት ሥርና ዘር ነኝ፣ የሚያበራም የንጋት ኮከብ ነኝ።”

ራእይ 22