7. የበጉ ሰርግ ስለ ደረሰ፣የእርሱም ሙሽራ ራሷን ስላዘጋጀች፣ደስ ይበለን፤ ሐሤት እናድርግክብርም እንስጠው።
8. የሚያንጸባርቅና ንጹሕ፣ከተልባ እግር የተሠራ ቀጭን ልብስ እንድትለብስ ተሰጣት።”ከተልባ እግር የተሠራው ቀጭን ልብስ የቅዱሳን የጽድቅ ሥራ ነው።
9. መልአኩም፣ “ ‘ወደ በጉ ሰርግ እራት የተጠሩ ብፁዓን ናቸው’ ብለህ ጻፍ” አለኝ፤ ቀጥሎም፣ “እነዚህ የእግዚአብሔር እውነተኛ ቃሎች ናቸው” አለኝ።
10. እኔም ልሰግድለት በእግሩ ሥር ተደፋሁ፤ እርሱ ግን፣ “ተው! ይህን አታድርግ! እኔም ከአንተና የኢየሱስን ምስክር ከያዙት ወንድሞችህ ጋር አገልጋይ ነኝ፤ ለእግዚአብሔር ስገድ፤ የኢየሱስ ምስክር የትንቢት መንፈስ ነውና” አለኝ።
11. ከዚያም ሰማይም ተከፍቶ አየሁ፤ እነሆ አንድ ነጭ ፈረስ ነበረ፤ በፈረሱም ላይ፣ “ታማኝና እውነተኛ” የሚባል ተቀምጦ ነበር፤ እርሱም በጽድቅ ይፈርዳል፤ ይዋጋልም።
12. ዐይኖቹ እንደ እሳት ነበልባል ናቸው፤ በራሱም ላይ ብዙ ዘውዶች አሉ። ከእርሱ በቀር ማንም የማያውቀው ስም በእርሱ ላይ ተጽፎአል።
13. እርሱ በደም የተነከረ ልብስ ለብሶአል፤ ስሙም የእግዚአብሔር ቃል ነው።
14. የሰማይም ሰራዊት ነጭ፣ ንጹሕና ከተልባ እግር የተሠራ ቀጭን ልብስ ለብሰው፣ በነጫጭ ፈረሶች ላይ ተቀምጠው ይከተሉት ነበር።