1. ዘንዶውም በባሕሩ ዳር ቆሞ ነበር።ከዚያም አንድ አውሬ ከባሕር ሲወጣ አየሁ፤ እርሱም ዐሥር ቀንዶችና ሰባት ራሶች ነበሩት፤ በቀንዶቹም ላይ ዐሥር ዘውዶች፣ በራሶቹም ላይ የስድብ ስሞች ነበሩት።
2. ያየሁትም አውሬ ነብር ይመስል ነበር፤ ነገር ግን እግሮቹ የድብ፣ አፉ ደግሞ የአንበሳ አፍ ይመስል ነበር፤ ዘንዶው የራሱን ኀይልና የራሱን ዙፋን እንዲሁም ታላቅ ሥልጣን ለአውሬው ሰጠው።
3. ከአውሬው ራሶች አንዱ ለሞት የሚያደርስ ቊስል ያለበት ይመስል ነበር። ነገር ግን ለሞት የሚያደርሰው ቊስሉ ዳነ፤ ዓለም በሙሉ በመደነቅ አውሬውን ተከተለው።