ራእይ 11:1-7 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ከዚያም ሸምበቆ የመሰለ መለኪያ በትር ተሰጠኝ፤ እንዲህም ተባልሁ፤ “ሄደህ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስና መሠዊያውን ለካ፤ በዚያም የሚያመልኩትን ቊጠር።

2. የውጭውን አደባባይ ግን ተወው፤ አትለካው፤ ለአሕዛብ የተሰጠ ነውና። እነርሱ የተቀደሰችውን ከተማ አርባ ሁለት ወር ይረግጧታል።

3. ለሁለቱ ምስክሮቼ ኀይል እሰጣቸዋለሁ፤ እነርሱም ማቅ ለብሰው አንድ ሺህ ሁለት መቶ ሥልሳ ቀን ትንቢት ይናገራሉ።”

4. እነዚህም በምድር ጌታ ፊት የሚቆሙት ሁለቱ የወይራ ዛፎችና ሁለቱ መቅረዞች ናቸው።

5. ማንም እነርሱን ሊጐዳ ቢፈልግ፣ እሳት ከአፋቸው ወጥቶ ጠላቶቻቸውን ያጠፋል፤ ሊጐዳቸው የሚፈልግ ሁሉ መሞት ያለበት በዚህ ዐይነት ነው።

6. እነዚህ ሰዎች ትንቢት በሚናገሩባቸው ወራት ዝናብ እንዳይዘንብ ሰማይን ለመዝጋት ሥልጣን አላቸው፤ ደግሞም ውሃዎችን ወደ ደም ለመለወጥ በሚፈልጉበት ጊዜ ሁሉ ምድርን በማንኛውም መቅሠፍት ለመምታት ሥልጣን አላቸው።

7. ምስክርነታቸውን ከጨረሱ በኋላ ከጥልቁ የሚወጣው አውሬ ይዋጋቸዋል፤ ድል ይነሣቸዋል፤ ይገድላቸዋልም።

ራእይ 11