1. ኑኃሚን፤ ከአቤሜሌክ ጐሣ የሆነ ቦዔዝ የሚባል ባለጸጋ የባል ዘመድ ነበራት።
2. ሞዓባዊቷ ሩትም ኑኃሚንን፣ “በፊቱ ሞገስ አግኝቼ ቃርሚያ የሚያስቃርመኝ ሰው ባገኝ እስቲ ወደ እህል አዝመራው ልሂድ” አለቻት።ኑኃሚንም፣ “ልጄ ሆይ፤ ይሁን ሂጂ” አለቻት።
3. ስለዚህ እርሷም ወጣች፤ ከአጫጆች ኋላ ኋላ እየተከታተለችም ከአዝመራው ቦታ ትቃርም ጀመር፤ እንዳጋጣሚ ትቃርምበት የነበረው አዝመራ ከአቤሜሌክ ጐሣ የሆነው የቦዔዝ ነበር።
4. በዚሁ ጊዜ ቦዔዝ ከቤተ ልሔም መጣ፤ አጫጆቹንም፣ “እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ይሁን” ብሎ ሰላምታ ሰጣቸው።እነርሱም፣ “እግዚአብሔር ይባርክህ” ብለው መለሱለት።
5. ከዚያም ቦዔዝ የአጫጆቹን አለቃ፣ “ይህች ወጣት ሴት የማን ናት?” ሲል ጠየቀው።