22. በምትሄድበት ሁሉ ይመሩሃል፤በምትተኛበት ጊዜ ይጠብቁሃል፤በምትነቃበት ጊዜም ያነጋግሩሃል።
23. እነዚህ ትእዛዞች መብራት ናቸውና፤ይህችም ትምህርት ብርሃን፣የተግሣጽ ዕርምትም የሕይወት መንገድ ናት፤
24. እርሷም ከምግባረ ብልሹ ሴት፣ልዝብ አንደበት ካላት ዘልዛላ ሴት ትጠብቅሃለች።
25. ውበቷን በልብህ አትመኝ፤በዐይኗም አትጠመድ፤
26. ጋለሞታ ሴት ቊራሽ እንጀራ ታሳጣሃለችና፤አመንዝራዪቱም በሕይወትህ በራሱ ላይ ትሸምቃለች።
27. ለመሆኑ ልብሱ ሳይቃጠል፣በጒያው እሳት መያዝ የሚችል ሰው አለን?
28. አንድ ሰው እግሮቹ ሳይቃጠሉ፣በፍም ላይ መሄድ ይችላልን?
29. ከሰው ሚስት ጋር የሚተኛም እንደዚሁ ነው፤የሚደርስባትም ከቅጣት አያመልጥም።
30. ሌባ በተራበ ጊዜ ራቡን ለማስታገሥ ቢሰርቅ፣ሰዎች አይንቁትም።
31. በቤቱ ያለውን ሀብት ሁሉ የሚጠይቀው ቢሆንም፣ከተያዘ ሰባት ዕጥፍ መክፈል አለበት።
32. የሚያመነዝር ሰው ግን ማመዛዘን ይጐድለዋል፤እንዲህ የሚያደርግ ሁሉ ራሱን ያጠፋል።
33. መደብደብና ውርደት ዕጣው ነው፤ኀፍረቱም ከቶ አይወገድም፤
34. ቅናት የባልን ቊጣ ይቀሰቅሳልና፤በሚበቀልበትም ጊዜ ምሕረት አያደርግም።