ምሳሌ 6:19-30 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

19. በውሸት ላይ ውሸት የሚጨምር ሐሰተኛ ምስክር፣በወንድማማቾች መካከል ጠብን የሚጭር ሰው።

20. ልጄ ሆይ፤ የአባትህን ትእዛዝ አክብር፤የእናትህንም ትምህርት አትተው።

21. ምንጊዜም በልብህ አኑራቸው፤በዐንገትህም ዙሪያ እሰራቸው።

22. በምትሄድበት ሁሉ ይመሩሃል፤በምትተኛበት ጊዜ ይጠብቁሃል፤በምትነቃበት ጊዜም ያነጋግሩሃል።

23. እነዚህ ትእዛዞች መብራት ናቸውና፤ይህችም ትምህርት ብርሃን፣የተግሣጽ ዕርምትም የሕይወት መንገድ ናት፤

24. እርሷም ከምግባረ ብልሹ ሴት፣ልዝብ አንደበት ካላት ዘልዛላ ሴት ትጠብቅሃለች።

25. ውበቷን በልብህ አትመኝ፤በዐይኗም አትጠመድ፤

26. ጋለሞታ ሴት ቊራሽ እንጀራ ታሳጣሃለችና፤አመንዝራዪቱም በሕይወትህ በራሱ ላይ ትሸምቃለች።

27. ለመሆኑ ልብሱ ሳይቃጠል፣በጒያው እሳት መያዝ የሚችል ሰው አለን?

28. አንድ ሰው እግሮቹ ሳይቃጠሉ፣በፍም ላይ መሄድ ይችላልን?

29. ከሰው ሚስት ጋር የሚተኛም እንደዚሁ ነው፤የሚደርስባትም ከቅጣት አያመልጥም።

30. ሌባ በተራበ ጊዜ ራቡን ለማስታገሥ ቢሰርቅ፣ሰዎች አይንቁትም።

ምሳሌ 6