ምሳሌ 5:6-19 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

6. ስለ ሕይወት መንገድ ደንታ የላትም፤መንገዶቿ ዘወርዋራ ናቸው፤ ለእርሷ ግን አይታወቃትም።

7. እንግዲህ፣ ልጆቼ ሆይ፤ አድምጡኝ፤ከምነግራችሁ ቃል ፈቀቅ አትበሉ።

8. መንገድህን ከእርሷ አርቅ፤በደጃፏም አትለፍ፤

9. ይኸውም ጒብዝናህን ለሌሎች፣ዕድሜህንም ለጨካኞች እንዳትሰጥ ነው፤

10. ባዕዳን በሀብትህ እንዳይፈነጥዙ፣ልፋትህም የሌላውን ሰው ቤት እንዳያበለጽግ ነው።

11. በዕድሜህ መጨረሻ ታቃሥታለህ፤ሥጋህና ሰውነትህ ሲከዳህ።

12. እንዲህም ትላለህ፤ “ምነው! ተግሣጽን ጠላሁ፤ልቤስ ምነው! መታረምን ናቀ፤

13. የመምህሮቼን ቃል አልሰማሁም፤አሰልጣኞቼንም አላደመጥኋቸውም፤

14. በመላው ጉባኤ ፊት፣ወደ ፍጹም ጥፋት ተቃርቤአለሁ።”

15. ከገዛ ማጠራቀሚያህ ውሃ፣ከገዛ ጒድጓድህም የሚፈልቀውን ውሃ ጠጣ።

16. ምንጮችህ ተርፈው ወደ ሜዳ፣ወንዞችህስ ወደ አደባባይ ሊፈሱ ይገባልን?

17. ለአንተ ብቻ ይሁኑ፤ባዕዳን አይጋሩህ።

18. ምንጭህ ቡሩክ ይሁን፤በልጅነት ሚስትህም ደስ ይበልህ።

19. እርሷ እንደ ተወደደች ዋላ፣ እንደ ተዋበች ሚዳቋ ናት፤ጡቶቿ ዘወትር ያርኩህ፤ፍቅሯም ሁል ጊዜ ይማርክህ።

ምሳሌ 5