1. የያቄ ልጅ የአጉር ቃል ይህ ነው፤ይህ ሰው ለኢቲኤል፣ለኢቲኤልና ለኡካል ተናገረ፤
2. “እኔ ከሰው ሁሉ ይልቅ ጅል ነኝ፤ሰው ያለው ማስተዋል የለኝም።
3. ጥበብን አልተማርሁም፤ስለ ቅዱሱም ዕውቀት የለኝም።
4. ወደ ሰማይ የወጣ፣ የወረደስ ማነው?ነፋስን በእጁ ሰብስቦ የያዘ ማነው?ውሆችንስ በመጐናጸፊያው የጠቀለለ ማነው?የምድርን ዳርቻዎች ሁሉ የወሰነ ማነው?ስሙ ማን ነው? የልጁስ ስም ማን ይባላል?የምታውቅ ከሆነ እስቲ ንገረኝ!
5. “የእግዚአብሔር ቃል ሁሉ እንከን የለበትም፤እርሱ ለሚታመኑበት ሁሉ ጋሻቸው ነው።
6. በእርሱ ቃል ላይ አንዳች አትጨምር፤አለዚያ ይዘልፍሃል፤ ሐሰተኛም ያደርግሃል።