ምሳሌ 28:14-27 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

14. እግዚአብሔርን ዘወትር የሚፈራ ሰው ቡሩክ ነው፤ልቡን የሚያደነድን ግን መከራ ላይ ይወድቃል።

15. ታዳጊ በሌለው ሕዝብ ላይ የተሾመ ጨካኝ ገዥ፣እንደሚያገሣ አንበሳ ወይም ተንደንድሮ እንደሚይዝ ድብ ነው።

16. ጨካኝ ገዥ ማመዛዘን ይጐድለዋል፤ያላግባብ የሚገኝን ጥቅም የሚጸየፍ ግን ዕድሜው ይረዝማል።

17. የሰው ደም ያለበት ሰው፣ዕድሜ ልኩን ሲቅበዘበዝ ይኖራል፤ማንም ሰው አይርዳው።

18. አካሄዱ ነቀፋ የሌለበት ሰው ክፉ አያገኘውም፤መንገዱ ጠማማ የሆነ ግን ድንገት ይወድቃል።

19. መሬቱን የሚያርስ የተትረፈረፈ ምግብ ያገኛል፤ከንቱ ተስፋን ይዞ የሚጓዝ ግን ድኽነትን ይወርሳል።

20. ታማኝ ሰው እጅግ ይባረካል፤ሀብት ለማግኘት የሚጣደፍ ግን ከቅጣት አያመልጥም።

21. አድልዎ ማድረግ መልካም አይደለም፤ሰው ግን ለቊራሽ እንጀራ ሲል በደል ይፈጽማል።

22. ስስታም ሀብት ለማከማቸት ይስገበገባል፤ድኽነት እንደሚጠብቀውም አያውቅም።

23. ሸንጋይ አንደበት ካለው ይልቅ፣ሰውን የሚገሥጽ ውሎ ዐድሮ ይወደዳል።

24. ከአባት ከእናቱ ሰርቆ፣“ይህ ጥፋት አይደለም” የሚል የአጥፊ ተባባሪ ነው።

25. ስስታም ሰው ጠብን ያነሣሣል፤ በእግዚአብሔር የሚታመን ግን ይባረካል።

26. በራሱ የሚታመን ተላላ ነው፤በጥበብ የሚመላለስ ግን ክፉ አያገኘውም።

27. ለድኾች የሚሰጥ አይቸገርም፤አይቶአቸው እንዳላየ የሚሆን ግን ብዙ ርግማን ይደርስበታል።

ምሳሌ 28