ምሳሌ 24:4-21 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

4. በዕውቀትም ውድና ውብ በሆነ ንብረት፣ክፍሎቹ ይሞላሉ።

5. ጠቢብ ሰው ታላቅ ኀይል አለው፤ዕውቀት ያለውም ሰው ብርታትን ይጨምራል፤

6. ጦርነት ለመግጠም መልካም ምክር፣ድል ለማድረግም ብዙ አማካሪዎች ያስፈልጋሉ።

7. ጥበብ ለተላላ በጣም ሩቅ ናት፤በከተማዪቱ በር ሸንጎ ላይም መናገር አይችልም።

8. ክፋት የሚያውጠነጥን፣‘ተንኰለኛ’ በመባል ይታወቃል።

9. የተላላ ዕቅድ ኀጢአት ነው፤ሰዎችም ፌዘኛን ይጸየፋሉ።

10. በመከራ ጊዜ ፈራ ተባ ካልህ፣ዐቅምህ ምንኛ ደካማ ነው!

11. ወደ ሞት የሚነዱትን ታደጋቸው፤እየተጐተቱ ለዕርድ የሚሄዱትን አድናቸው።

12. አንተም፣ “ስለዚህ ነገር ምንም አላውቅም” ብትል፣ልብን የሚመረምር እርሱ አያስተውልምን?ሕይወትህን የሚጠብቃት እርሱ አያውቅምን?ለእያንዳንዱስ እንደ ሥራው መጠን አይከፍለውምን?

13. ልጄ ሆይ፤ መልካም ነውና ማር ብላ፤የማር ወለላም ጣዕም ይጣፍጥሃል።

14. ጥበብም ለነፍስህ እንደዚሁ ጣፋጭ እንደሆነች ዕወቅ፤ብታገኛት ለነገ አለኝታ ይኖርሃል፤ተስፋህም ከንቱ አይሆንም።

15. በጻድቅ ሰው ቤት ላይ እንደ ወንበዴ አታድፍጥ፤መኖሪያውንም በድንገት አታጥቃ፤

16. ጻድቅ ሰባት ጊዜ እንኳ ቢወድቅ ይነሣልና፤ክፉዎች ግን በጥፋት ይወድቃሉ።

17. ጠላትህ ሲወድቅ ደስ አይበልህ፤ሲሰናከልም ልብህ ሐሤት አያድርግ፤

18. አለዚያ እግዚአብሔር ይህን አይቶ ደስ አይለውም፤ቍጣውንም ከእርሱ ይመልሳል።

19. በጨካኞች ድርጊት አትጨነቅ፤በክፉዎችም አትቅና፤

20. ግፈኛ ተስፋ የለውምና፤የክፉዎችም መብራት ድርግም ብላ ትጠፋለች።

21. ልጄ ሆይ፤ እግዚአብሔርንና ንጉሥን ፍራ፤ከዐመፀኞችም ጋር አትተባበር፤

ምሳሌ 24