ምሳሌ 23:4-18 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

4. ሀብት ለማግኘት ስትል ራስህን አታድክም፤ሐሳብህን የመግታት ጥበብ ይኑርህ።

5. በሀብት ላይ ዐይንህን ብትጥል፤ወዲያው ይጠፋል፤ወደ ሰማይ እንደሚበርር ንስር፣ በርግጥ ክንፍ አውጥቶ ይበራል፤

6. የስስታምን ምግብ አትብላ፤ጣፋጭ መብሉም አያስጐምጅህ፤

7. ሁል ጊዜ ስለ ዋጋ የሚያሰላ ሰው ነውና፤“ብላ፣ ጠጣ” ይልሃል፤ልቡ ግን ከአንተ ጋር አይደለም።

8. የበላሃት ትንሿ እንኳ ታስመልስሃለች፤የምስጋና ቃልህንም ከንቱ ታደርጋለህ።

9. ከጅል ጋር አትነጋገር፤የቃልህን ጥበብ ያንኳስሳልና።

10. የጥንቱን የወሰን ምልክት አታፋልስ፤አባት የሌላቸውንም ልጆች መሬት አትግፋ፤

11. ታዳጊያቸው ብርቱ ነውና፤እርሱ ይፋረድላቸዋል።

12. ልብህን ለምክር፣ጆሮህንም ለዕውቀት ቃል ስጥ።

13. ልጅን ከመቅጣት ወደ ኋላ አትበል፤በአርጩሜ ብትገርፈው አይሞትም።

14. በአርጩሜ ቅጣው፤ነፍሱንም ከሞት አድናት።

15. ልጄ ሆይ፤ ልብህ ጠቢብ ቢሆን፣የእኔም ልብ ሐሤት ያደርጋል፤

16. ከንፈሮችህ ትክክሉን ቢናገሩ፣ውስጣዊ ሁለንተናዬ ሐሤት ያደርጋል።

17. ልብህ በኀጢአተኞች አይቅና፤ነገር ግን ዘወትር እግዚአብሔርን ለመፍራት ትጋ።

18. ለነገ ርግጠኛ አለኝታ ይኖርሃል፤ተስፋህም ከንቱ አይሆንም።

ምሳሌ 23