1. የንጉሥ ልብ በእግዚአብሔር እጅ ነው፤እርሱም እንደ ቦይ ውሃ ደስ ወዳሰኘው ይመራዋል።
2. ለሰው መንገዱ ሁሉ ቀና ይመስለዋል፤ እግዚአብሔር ግን ልብን ይመዝናል።
3. ከመሥዋዕት ይልቅ ጽድቅንና ፍትሕን ማድረግ፣ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት አለው።
4. ትዕቢተኛ ዐይን፣ እብሪተኛ ልብ፣የክፉዎችም መብራት ኀጢአት ናቸው።
5. የትጒህ ሰው ዕቅድ ወደ ትርፍ ያመራል፤ችኰላም ወደ ድኽነት ያደርሳል።
6. በሐሰተኛ አንደበት የተገኘ ሀብት፣በኖ የሚጠፋ ተን፣ ለሞትም የሚያበቃ ወጥመድ ነው።
7. ክፉዎችን ዐመፃቸው ይጠራርጋቸዋል፤ቅን ነገር ማድረግ አይወዱምና።
8. የበደለኛ መንገድ ጠማማ ነው፤የንጹሕ ሰው ጠባይ ግን ቀና ነው።
9. ከጨቅጫቃ ሚስት ጋር በአንድ ቤት ከመኖር፣በጣራ ላይ ጥግ ይዞ መኖር ይሻላል።
10. ክፉ ሰው ክፋትን አጥብቆ ይመኛል፤ባልንጀራውም ከእርሱ ዘንድ ርኅራኄን አያገኝም።
11. ፌዘኛ ሲቀጣ፣ አላዋቂ ጥበብን ያተርፋል፤ጠቢብ ሰው ቢማር ዕውቀትን ያገኛል።
12. ጻድቁ የክፉዎችን ቤት ልብ ብሎ ይመለከታል፤ክፉዎችንም ያጠፋቸዋል።
13. ሰው የድኾችን ጩኸት ላለመስማት ጆሮውን ቢዘጋ፣እርሱም ይጮኻል፤ መልስም አያገኝም።
14. በስውር የተደረገ ስጦታ ቊጣን ያበርዳል፤በጒያ የተሸሸገ እጅ መንሻም ታላቅ ቊጣን ጸጥ ያደርጋል።
15. ፍትሕ ሲሰፍን ጻድቁን ደስ ያሰኘዋል፤ክፉ አድራጊዎችን ግን ያሸብራል።
16. የማስተዋልን መንገድ የሚስት ሰው፣በሙታን ጉባኤ ያርፋል።
17. ቅንጦትን የሚወድ ይደኸያል፤የወይን ጠጅና ዘይት የሚወድም ባለጠጋ አይሆንም።
18. ክፉ ሰው ለጻድቅ፣ወስላታም ለቅን ሰው ወጆ ይሆናል።
19. ከጨቅጫቃና ከቊጡ ሚስት ጋር ከመኖር፣በምድረ በዳ መኖር ይሻላል።