ምሳሌ 20:17-27 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

17. ሰው በማጭበርበር ያገኘው ምግብ ይጣፍጠዋል፤በመጨረሻ ግን አፉን ኰረት ሞልቶት ያገኘዋል።

18. ምክር ጠይቀህ ዕቅድ አውጣ፤ጦርነት የምትገጥም ከሆነ መመሪያ ተቀበል።

19. ሐሜተኛ ምስጢር ያባክናል፤ስለዚህ ለፍላፊን ሰው አርቀው።

20. አባቱን ወይም እናቱን የሚሰድብ፣መብራቱ በድቅድቅ ጨለማ ይጠፋል።

21. ከጅምሩ ወዲያው የተገኘ ርስት፣በመጨረሻ በረከት አይኖረውም።

22. “ለደረሰብኝ በደል ብድሬን ባልመልስ!” አትበል፤ እግዚአብሔርን ጠብቅ፤ እርሱ ይታደግሃል።

23. ሁለት ዐይነት ሚዛን በእግዚአብሔር ዘንድ አጸያፊ ነው፤ዐባይ ሚዛን አይወደድም።

24. የሰው አካሄዱ በእግዚአብሔር ይመራል፤ሰውስ የገዛ መንገዱን እንዴት ማስተዋል ይችላል?

25. በችኰላ ስእለት መሳል፣ከተሳሉም በኋላ ማቅማማት ለሰው ወጥመድ ነው።

26. ጠቢብ ንጉሥ ክፉዎችን አበጥሮ ይለያል፤የመውቂያ መንኰራኵርንም በላያቸው ላይ ይነዳል።

27. የሰው መንፈስ ለእግዚአብሔር መብራት ነው፤ውስጣዊ ማንነቱንም ይፈትሻል።

ምሳሌ 20