1. የወይን ጠጅ ፌዘኛ፣ ብርቱ መጠጥም ጠበኛ ያደርጋል፤በእነዚህ የሳተ ሁሉ ጠቢብ አይደለም።
2. የንጉሥ ቊጣ እንደ አንበሳ ግሣት ነው፤የሚያስቈጣውም ሰው ሕይወቱን ለመከራ ይዳርጋል።
3. ከጠብ መራቅ ለሰው ክብሩ ነው፤ተላላ ሁሉ ግን ለጥል ይቸኵላል።
4. ሰነፍ ሰው በወቅቱ አያርስም፤ስለዚህ በመከር ወራት ይፈልጋል፤አንዳችም አያገኝም።
5. የሰው ልብ ሐሳብ እንደ ጥልቅ ውሃ ነው፤አስተዋይ ሰው ግን ከዚያ ቀድቶ ያወጣዋል።
6. ብዙ ሰው ጽኑ ፍቅር እንዳለው ይናገራል፤ታማኝን ሰው ግን ማን ሊያገኘው ይችላል?
7. ጻድቅ ነቀፋ የሌለበት ሕይወት ይመራል፤ከእርሱም በኋላ የሚከተሉት ልጆቹ ቡሩካን ናቸው።
8. ንጉሥ ለፍርድ ዙፋኑ ላይ በሚቀመጥበት ጊዜ፣ክፉውን ሁሉ በዐይኖቹ አበጥሮ ይለያል።
9. ለመሆኑ፣ “ልቤን በንጽሕና ጠብቄአለሁ፤ንጹሕ ነኝ፤ ኀጢአት የለብኝም” የሚል ማን ነው?
10. ሁለት ዐይነት ሚዛን፣ ሁለት ዐይነት መስፈሪያ፣ሁለቱንም እግዚአብሔር ይጸየፋቸዋል።
11. ሕፃን እንኳ ጠባዩ ንጹሕና ቅን መሆኑ፣ከአድራጎቱ ይታወቃል።