ምሳሌ 15:3-16 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

3. የእግዚአብሔር ዐይኖች በሁሉም ስፍራ ናቸው፤ክፉዎችንም ደጎችንም ነቅተው ይመለከታሉ።

4. ፈውስ የምታመጣ ምላስ የሕይወት ዛፍ ናት፤አታላይ ምላስ ግን መንፈስን ትሰብራለች።

5. ተላላ የአባቱን ምክር ይንቃል፤መታረምን የሚቀበል ግን አስተዋይነቱን ያሳያል።

6. የጻድቃን ቤት በብዙ ሀብት የተሞላ ነው፤የክፉዎች ገቢ ግን መከራን ታመጣባቸዋለች።

7. የጠቢባን ከንፈር ዕውቀትን ታስፋፋለች፤የተላሎች ልብ ግን እንዲህ አይደለም።

8. እግዚአብሔር የክፉዎችን መሥዋዕት ይጸየፋል፤የቅኖች ጸሎት ግን ደስ ያሰኘዋል።

9. እግዚአብሔር የክፉዎችን መንገድ ይጸየፋል፤ጽድቅን የሚከታተሉትን ግን ይወዳቸዋል።

10. ከመንገድ የሚወጣ ሰው ጥብቅ ቅጣት ይጠብቀዋል፤ዕርምትን የሚጠላ ይሞታል።

11. ሲኦልና የሙታን ዓለም በእግዚአብሔር ፊት የተገለጡ ናቸው፤የሰዎች ልብ ማየቱን ያህል የታወቀ ነው!

12. ፌዘኛ መታረምን ይጠላል፤ጠቢባንንም አያማክርም።

13. ደስተኛ ልብ ፊትን ያፈካል፤የልብ ሐዘን ግን መንፈስን ይሰብራል።

14. አስተዋይ ልብ ዕውቀትን ይሻል፤የተላላ አፍ ግን ቂልነትን ያመነዥካል።

15. የተጨቈኑ ሰዎች ዘመናቸው ሁሉ የከፋ ነው፤በደስታ የተሞላ ልብ ግን የማይቋረጥ ፈንጠዝያ አለው።

16. እግዚአብሔርን ከመፍራት ጋር ያለ ጥቂት ነገር፣ሁከት ካለበት ትልቅ ሀብት ይበልጣል።

ምሳሌ 15