ምሳሌ 15:11-26 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

11. ሲኦልና የሙታን ዓለም በእግዚአብሔር ፊት የተገለጡ ናቸው፤የሰዎች ልብ ማየቱን ያህል የታወቀ ነው!

12. ፌዘኛ መታረምን ይጠላል፤ጠቢባንንም አያማክርም።

13. ደስተኛ ልብ ፊትን ያፈካል፤የልብ ሐዘን ግን መንፈስን ይሰብራል።

14. አስተዋይ ልብ ዕውቀትን ይሻል፤የተላላ አፍ ግን ቂልነትን ያመነዥካል።

15. የተጨቈኑ ሰዎች ዘመናቸው ሁሉ የከፋ ነው፤በደስታ የተሞላ ልብ ግን የማይቋረጥ ፈንጠዝያ አለው።

16. እግዚአብሔርን ከመፍራት ጋር ያለ ጥቂት ነገር፣ሁከት ካለበት ትልቅ ሀብት ይበልጣል።

17. ፍቅር ባለበት ጐመን መብላት፣ጥላቻ ባለበት የሰባ ፍሪዳ ከመብላት ይሻላል።

18. ግልፍተኛ ሰው ጠብ ያነሣሣል፤ታጋሽ ሰው ግን ጠብን ያበርዳል።

19. የሀኬተኛ መንገድ በእሾህ የታጠረች ናት፤የቅኖች መንገድ ግን የተጠረገ አውራ ጐዳና ነው።

20. ጠቢብ ልጅ አባቱን ደስ ያሰኛል፤ተላላ ሰው ግን እናቱን ይንቃል።

21. ማመዛዘን የጐደለው ሰው ቂልነት ያስደስተዋል፤አስተዋይ ሰው ግን ቀጥተኛውን መንገድ ይከተላል።

22. ምክር ሲጓደል ዕቅድ ይፋለሳል፤በብዙ አማካሪዎች ግን ይሳካል።

23. ሰው ተገቢ መልስ በመስጠት ደስታን ያገኛል፤በወቅቱም የተሰጠ ቃል ምንኛ መልካም ነው!

24. ወደ ሲኦል ከመውረድ እንዲድን፣የሕይወት መንገድ ጠቢቡን ሰው ወደ ላይ ትመራዋለች።

25. እግዚአብሔር የትዕቢተኛውን ቤት ያፈርሰዋል፤የመበለቲቱን ዳር ድንበር ግን እንዳይደፈር ይጠብቃል።

26. እግዚአብሔር የክፉውን ሰው ሐሳብ ይጸየፋል፤የንጹሓን ሐሳብ ግን ደስ ያሰኘዋል።

ምሳሌ 15