ምሳሌ 14:1-13 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ጠቢብ ሴት ቤቷን ትሠራለች፤ተላላ ሴት ግን በገዛ እጇ ታፈርሰዋለች።

2. አካሄዱ ቅን የሆነ ሰው እግዚአብሔርን ይፈራል፤መንገዱ ጠማማ የሆነ ግን ይንቀዋል።

3. የተላላ ሰው ንግግር ለጀርባው በትር ታስከትልበታለች፤የጥበበኛ ከንፈር ግን ትጠብቃቸዋለች።

4. በሬዎች በሌሉበት ገንዳው ባዶ ይሆናል፤በበሬ ጒልበት ግን ብዙ ምርት ይገኛል።

5. ታማኝ ምስክር አይዋሽም፤ሐሰተኛ ምስክር ግን ውሸትን ይዘከዝካል።

6. ፌዘኛ ጥበብን ይሻል፤ ሆኖም አያገኛትም፤ዕውቀት ግን ለአስተዋዮች በቀላሉ ትገኛለች።

7. ከተላላ ሰው ራቅ፤ከከንፈሮቹ ዕውቀት አታገኝምና።

8. የአስተዋዮች ጥበብ መንገዳቸውን ልብ ማለት ነው፤የተላሎች ሞኝነት ግን መታለል ነው።

9. ተላሎች በሚያቀርቡት የበደል ካሳ ያፌዛሉ፤በቅኖች መካከል ግን በጎ ፈቃድ ትገኛለች።

10. እያንዳንዱ ልብ የራሱን መራራ ሐዘን ያውቃል፤ደስታውንም ማንም ሊጋራው አይችልም።

11. የክፉዎች ቤት ይፈርሳል፤የቅኖች ድንኳን ግን ይስፋፋል።

12. ለሰው ቀና መስሎ የሚታይ መንገድ አለ፤በመጨረሻ ግን ወደ ሞት ያደርሳል።

13. በሣቅ ጊዜ እንኳ ልብ ይተክዛል፤ደስታም በሐዘን ሊፈጸም ይችላል።

ምሳሌ 14